የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ሮም ሰዎች 3:21-31

ወደ ሮም ሰዎች 3:21-31 አማ05

አሁን ግን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበት መንገድ ያለ ሕግ መሆኑ ተገልጦአል፤ ይህም በሙሴ ሕግና በነቢያት ተመስክሮአል። ስለዚህ እግዚአብሔር ምንም ልዩነት ሳያደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ጽድቅን ይሰጣል። ሰዎች ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋል፤ እግዚአብሔር የሰጣቸውንም ክብር አጥተዋል። ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው በአዳኝነት ሥራ በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ይጸድቃሉ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በደሙ የኃጢአታቸውን ስርየት እንዲያገኙ ነው፤ እግዚአብሔር ይህን ማድረጉ በትዕግሥቱ የቀድሞውን ኃጢአት እንዳልነበረ በማድረግ የራሱን ትክክለኛ ፍርድ ለመግለጥ ነው። በአሁኑም ዘመን እግዚአብሔር ራሱ ጻድቅ መሆኑን የሚያሳየው በኢየሱስ የሚያምኑትን ሁሉ በማጽደቅ ነው። እንግዲህ የምንመካበት ነገር ምን አለ? በምንም አንመካም! የማንመካበትስ ምክንያት ምንድን ነው? ሕግን ስለምንፈጽም ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በእምነት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን የሚያጸድቀው፥ ሰው የሕግን ሥራ በመፈጸሙ ሳይሆን በእምነት መሆኑን እንገነዘባለን። ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? በእርግጥ የአሕዛብም አምላክ ነው። እግዚአብሔር አንድ ነው፤ አይሁድንም ሆነ አሕዛብን በእምነት የሚያጸድቅ እርሱ ነው። ታዲያ፥ በእምነት ምክንያት ሕግን እንሽራለን ማለት ነውን? አይደለም፤ ይልቅስ ሕግን አጥብቀን እንይዛለን።