የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ሮም ሰዎች 14:1-23

ወደ ሮም ሰዎች 14:1-23 አማ05

በእናንተ መካከል በእምነቱ ደካማ የሆነውን ሰው ተቀበሉት እንጂ በግል ሐሳቡ ላይ ክርክር አታንሡ። ለምሳሌ አንድ ሰው ማንኛውንም ነገር ለመብላት የሚያስችል እምነት ይኖረዋል፤ በእምነቱ ያልጸናው ሰው ግን አትክልት ብቻ ይበላል፤ ስለዚህ ማንኛውንም ነገር የሚበላ ሰው የማይበላውን ሰው አይንቀፈው፤ የማይበላውም በሚበላው ሰው ላይ አይፍረድ፤ እርሱንም እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። ታዲያ፥ በሌላ ሰው አገልጋይ ላይ የምትፈርድ አንተ ማነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ የጌታው ጉዳይ ነው። እንዲያውም እግዚአብሔር ሊያቆመው ስለሚችል ጸንቶ ይቆማል። እንዲሁም አንዱ ቀን ከሌላው ቀን ይበልጥ ክቡር ነው ብሎ የሚያስብ ይኖር ይሆናል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል ክብር አላቸው እንጂ በቀኖች መካከል ልዩነት የለም ብሎ ያስባል። እንግዲህ ይህን በመሳሰለው ነገር እያንዳንዱ ሰው ከልቡ ያመነበትን ያድርግ። አንዱን ቀን ከሌላው ቀን አስበልጦ የሚያከብር ቢኖር ይህን ማድረጉ ለጌታ ክብር ብሎ ነው፤ ማንኛውንም ምግብ የሚበላ ለጌታ ክብር ብሎ ይበላል፤ ስለሚበላውም ምግብ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፤ ማንኛውንም ምግብ የማይበላ ለጌታ ክብር ብሎ አይበላም፤ ባለመብላቱም እግዚአብሔርን ያመሰግናል። ከእኛ እያንዳንዱ ሕይወቱም ሆነ ሞቱ የራሱ አይደለም። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም፥ ብንሞትም የጌታ ነን። ስለዚህ ክርስቶስ ሞቶ ከሞት የተነሣው የሕያዋንና የሙታን ጌታ ለመሆን ነው። ታዲያ፥ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ወይስ ወንድምህን ለምን ትንቀዋለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን። ምክንያቱም፦ “እኔ ሕያው ነኝ ይላል እግዚአብሔር፤ ሰው ሁሉ በጒልበቱ በእኔ ፊት ይንበረከካል፤ በአንደበቱም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ይመሰክራል” ተብሎ ተጽፎአል። ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ቀርበን መልስ እንሰጣለን። ስለዚህ አንዳችን በአንዳችን ላይ አንፍረድ፤ ነገር ግን ማንም ሰው በወንድሙ መንገድ መሰናክል ወይም እንቅፋት ላለማኖር ይጠንቀቅ። አንድን ነገር ርኩስ ነው ብሎ ለሚያስብ ሰው ያ ነገር ለእርሱ ርኩስ ይሆንበታል እንጂ ማንኛውም ነገር በራሱ ርኩስ እንዳልሆነ እኔ በጌታ ኢየሱስ ዐውቄ አረጋግጣለሁ። አንተ በምትበላው ምግብ ምክንያት ለወንድምህ እንቅፋት ከሆንክ በፍቅር የምትኖር አይደለህም፤ ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለትን ሰው በምትበላው ምግብ ምክንያት እንዲጠፋ አታድርግ። እንግዲህ በእናንተ ዘንድ መልካም የሆነውን ነገር ሌሎች እንዲነቅፉት አታድርጉ። የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጽድቅ፥ ሰላምና ደስታ ነው እንጂ የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለም። በዚህ ሁኔታ ክርስቶስን የሚያገለግል ሰው እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል፤ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው። ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንታነጽበትን ነገር እንከተል። በምግብም ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አናፍርስ። ምግብ ሁሉ ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ሌላውን ሰው የሚያሰናክል ምግብ መብላት ስሕተት ነው። ስለዚህ ወንድምህን ላለማሰናከል ሥጋን አለመብላት፥ የወይን ጠጅን አለመጠጣት፥ ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ መልካም ነው። እንግዲህ ይህ እምነትህ በአንተና በእግዚአብሔር መካከል ይሁን፤ ትክክል ነው ብሎ የሚያምንበትን ነገር ሲያደርግ ኅሊናው የማይወቅሰው ሰው የተመሰገነ ነው። እየተጠራጠረ የሚበላ ሰው ግን ድርጊቱ በእምነት ላይ የተመሠረተ ስላልሆነ ይፈረድበታል፤ በእምነት ያልተደረገ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው።