የዮሐንስ ራእይ 22
22
1ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብሩህ መስተዋት ጥርት ያለውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤ #ሕዝ. 47፥1፤ ዘካ. 14፥8። 2ይህ ወንዝ በከተማይቱ ዋና መንገድ መካከል ሰንጥቆ ያልፋል፤ በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ በዓመት ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦችን ለመፈወስ ያገለግላሉ። #ዘፍ. 2፥9፤ ሕዝ. 47፥12። 3ከእንግዲህም ወዲህ ምንም ዐይነት ርግማን አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማይቱ ውስጥ ይሆናል፤ አገልጋዮቹም ያመልኩታል። #ዘካ. 14፥11። 4ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በየግምባራቸው ላይ ይሆናል። 5ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ። #ኢሳ. 60፥19፤ ዳን. 7፥18።
የኢየሱስ ተመልሶ መምጣት
6ከዚህ በኋላ መልአኩ እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ቃላት የታመኑና እውነተኞች ናቸው፤ ነቢያትን የሚያናግር አምላክ በቅርብ ጊዜ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ ለመግለጥ መልአኩን ላከ።”
7ኢየሱስም “እነሆ! እኔ በቶሎ እመጣለሁ! የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ የተመሰገነ ነው!” አለ።
8እነዚህን ነገሮች የሰማሁና ያየሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ፤ እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ላሳየኝ መልአክ ልሰግድለት በእግሩ ሥር ወደቅኩ። 9መልአኩ ግን “ተው ይህን አታድርግ! እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት ጋር የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ!” አለኝ። 10ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፤ “ጊዜው የቀረበ ስለ ሆነ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፤ 11ከእንግዲህ ወዲህ ዐመፀኛው ማመፁን ይቀጥል፤ ርኩሱም ይርከስ፤ ጻድቁም ይጽደቅ፤ ቅዱሱም ይቀደስ።” #ዳን. 12፥10።
12“እነሆ! እኔ በቶሎ እመጣለሁ! ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የምሰጠውን ዋጋ ይዤአለሁ፤ #ኢሳ. 40፥10፤ 62፥11፤ መዝ. 28፥4፤ ኤር. 17፥10። 13አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” #ራዕ. 1፥8፤17፤ 2፥8፤ ኢሳ. 44፥6፤ 48፥12።
14ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ለመብላትና በደጃፎችዋም ወደ ከተማይቱ ለመግባት መብት እንዲኖራቸው ልብሳቸውን ያጠቡ የተባረኩ ናቸው። #ዘፍ. 2፥9፤ 3፥22። 15እንደ ውሻ የሚልከፈከፉ፥ አስማተኞች፥ አመንዝሮች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖት አምላኪዎች፥ ውሸትን የሚወዱና በሐሰት መንገድ የሚሄዱ ሁሉ ከከተማይቱ ውጪ ይሆናሉ።
16“እኔ ኢየሱስ ይህን ምስክርነት እንዲሰጣችሁ መልአኬን ለአብያተ ክርስቲያን ልኬአለሁ፤ እኔ የዳዊት የትውልድ ሐረግና ዘር ነኝ፤ የሚያበራ የንጋት ኮከብ ነኝ።” #ኢሳ. 11፥1፤10።
17መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም “ና!” ይበል፤ የተጠማም ይምጣ፤ የፈለገም የሕይወትን ውሃ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ ይጠጣ። #ኢሳ. 55፥1።
18እነሆ፥ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ነገር ቢጨምር፥ በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች እግዚአብሔር ይጨምርበታል። 19ማንም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ነገር ቢያጐድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተነገሩት ከሕይወት ዛፍ ፍሬና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ድርሻውን ያጐድልበታል። #ዘዳ. 4፥2፤ 12፥32።
20የእነዚህ ነገሮች ምስክር የሆነው “በእርግጥ፥ በቶሎ እመጣለሁ!” ይላል።
አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!
21የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። #22፥21 ከሁላችሁ፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “ከሁሉ” ሲሉ ሌሎች “ከእግዚአብሔር ሕዝብ” ይላሉ፤ “ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ” የሚሉም አሉ።
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 22: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997