የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 20:1-15

የዮሐንስ ራእይ 20:1-15 አማ05

ከዚህ በኋላ የጥልቁን ጒድጓድ መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ዘንዶውንም ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው፤ ይህም ዘንዶ ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን የሚባለው የቀድሞው እባብ ነው፤ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሕዝቦችን እንዳያስት መልአኩ ዘንዶውን ወደ ጥልቁ ጒድጓድ ጣለው፤ ዘግቶም በማኅተም አሸገው፤ ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ መፈታት ይገባዋል። ከዚህ በኋላ ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ የመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ተቀምጠው አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ በመመስከራቸውና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሶች አየሁ፤ እነርሱ ለአውሬውና ለምስሉ ያልሰገዱ፥ ምልክቱንም በግንባራቸውም ሆነ በእጃቸው ላይ ያላደረጉ ናቸው፤ እነርሱ ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ። የቀሩት ሙታን ግን ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም፤ ይህም የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው፤ የመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆኑ የተመሰገኑና ቅዱሳን ናቸው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ እነርሱ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ። ሺህ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በዓለም ሁሉ የሚገኙትን ሕዝቦች ማለት ጎግንና ማጎግን ሊያስትና ለጦርነትም ሊያስከትት ይወጣል፤ ቊጥራቸው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነው፤ እነርሱ ወደ ምድር ሁሉ ተሠራጭተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በማቃጠል ደመሰሳቸው። ያሳታቸው ዲያብሎስ፥ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት በዲን በሚቃጠል እሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ፤ በዚያም ሌሊትና ቀን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሠቃያሉ። ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በዙፋኑም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም፤ ታናናሾችንና ታላላቆችን ሙታን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ የሕይወት መጽሐፍ የሆነ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው ሥራቸው መሠረት ፍርድ ተቀበሉ፤ ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም ሰው በሥራው መሠረት ፍርድ ተቀበለ። ሞትና ሲኦልም ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው፤ ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ተጣለ።