የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 20

20
የሺህ ዓመቱ መንግሥት
1ከዚህ በኋላ የጥልቁን ጒድጓድ መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ 2ዘንዶውንም ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው፤ ይህም ዘንዶ ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን የሚባለው የቀድሞው እባብ ነው፤ #ዘፍ. 3፥1። 3ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሕዝቦችን እንዳያስት መልአኩ ዘንዶውን ወደ ጥልቁ ጒድጓድ ጣለው፤ ዘግቶም በማኅተም አሸገው፤ ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ መፈታት ይገባዋል።
4ከዚህ በኋላ ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ የመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ተቀምጠው አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ በመመስከራቸውና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሶች አየሁ፤ እነርሱ ለአውሬውና ለምስሉ ያልሰገዱ፥ ምልክቱንም በግንባራቸውም ሆነ በእጃቸው ላይ ያላደረጉ ናቸው፤ እነርሱ ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ። #ዳን. 7፥9፤22። 5የቀሩት ሙታን ግን ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም፤ ይህም የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው፤ 6የመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆኑ የተመሰገኑና ቅዱሳን ናቸው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ እነርሱ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።
የሰይጣን መሸነፍ
7ሺህ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ 8በዓለም ሁሉ የሚገኙትን ሕዝቦች ማለት ጎግንና ማጎግን ሊያስትና ለጦርነትም ሊያስከትት ይወጣል፤ ቊጥራቸው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነው፤ #ሕዝ. 7፥2፤ 38፥2። 9እነርሱ ወደ ምድር ሁሉ ተሠራጭተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በማቃጠል ደመሰሳቸው። 10ያሳታቸው ዲያብሎስ፥ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት በዲን በሚቃጠል እሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ፤ በዚያም ሌሊትና ቀን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሠቃያሉ።
የመጨረሻ ፍርድ
11ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በዙፋኑም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም፤ 12ታናናሾችንና ታላላቆችን ሙታን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ የሕይወት መጽሐፍ የሆነ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው ሥራቸው መሠረት ፍርድ ተቀበሉ፤ #ዳን. 7፥9-10። 13ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም ሰው በሥራው መሠረት ፍርድ ተቀበለ። 14ሞትና ሲኦልም ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው፤ 15ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ተጣለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ