የዮሐንስ ራእይ 2:18-29

የዮሐንስ ራእይ 2:18-29 አማ05

“ለትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ “ይህ የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ዐይኖች ካሉትና በእሳት ፍም የነጠረ ናስ የሚመስሉ እግሮች ካሉት፥ ከእግዚአብሔር ልጅ የተነገረ ነው፤ ሥራህንና ፍቅርህን፥ እምነትህንና አገልግሎትህን፥ በትዕግሥት መጽናትህንም ዐውቃለሁ፤ የኋለኛው ሥራህ ከፊተኛው እንደሚበልጥም ዐውቃለሁ። ነገር ግን አንድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም ‘ነቢይት ነኝ’ የምትለዋን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ብለህ ታግሠሃታል፤ እርስዋ አገልጋዮቼ እንዲሴስኑና ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉ በማስተማር አሳስታቸዋለች። ንስሓ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ እርስዋ ግን ከዝሙትዋ ንስሓ መግባትን አልፈለገችም። ስለዚህ በሥቃይ አልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርስዋ ጋር ከሠሩት ከክፉ ሥራቸው ንስሓ ገብተው ካልተመለሱ በቀር ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩትንም ሁሉ ብርቱ ሥቃይ አመጣባቸዋለሁ፤ ልጆችዋንም በሞት እቀጣለሁ፤ አብያተ ክርስቲያንም ሁሉ የሰውን ሐሳብና ምኞት የምመረምር እኔ መሆኔን ያውቃሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደየሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። “በትያጥሮን ላላችሁትና ይህን መጥፎ ትምህርት ላልተቀበላችሁት ሁሉ፥ እንዲሁም አንዳንዶች ‘የሰይጣን ጥልቅ ምሥጢር ነው’ የሚሉትን ላልተከተላችሁ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፤ ሆኖም እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ። ድል ለሚነሣ፥ በሥራዬም ላይ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በአሕዛብ ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤ ‘በብረትም በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ቀጥቅጦ ያደቃቸዋል፤’ ይህም ሥልጣን እኔ ከአባቴ እንደ ተቀበልኩት ዐይነት ነው፤ የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!