የዮሐንስ ራእይ 2:12-17

የዮሐንስ ራእይ 2:12-17 አማ05

“ለጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ በሁለት በኩል ስለት ያለውን ሰይፍ ከያዘው የተነገረ ነው፤ አንተ የሰይጣን ዙፋን ባለበት ስፍራ መኖርህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል፤ በእኔ ላይ ያለህን እምነት አልካድክም፤ ታማኝ ምስክሬ የነበረው አንቲጳስ ሰይጣን በሚኖርበት በእናንተ ከተማ በተገደለ ጊዜ እንኳ በእኔ ማመንህን አልተውክም። ነገር ግን የምነቅፍብህ አንዳንድ ነገሮች አሉኝ፤ ይኸውም የበለዓምን ትምህርት የያዙ አንዳንድ ሰዎች በመካከላችሁ አሉ፤ ይህ በለዓም የእስራኤል ሕዝብ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ በመብላትና ዝሙት በማድረግ እንዲሰናከሉ ባላቅን የመከረ ነው። እንዲሁም የኒቆላውያንን ትምህርት የያዙ ሰዎችም በመካከላችሁ አሉ፤ ስለዚህ ንስሓ ግባ፤ አለበለዚያ በቶሎ ወደ አንተ መጥቼ እንደ ሰይፍ ባለው ከአፌ በሚወጣው ቃል እዋጋቸዋለሁ። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! ድል ለሚነሣ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፤ አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይም እሰጠዋለሁ፤ ከተቀባዩ በቀር ይህን ሌላ ማንም አያውቀውም።