የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 19

19
1ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል የብዙ ሰዎችን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ በሰማይ ሰማሁ “ሃሌ ሉያ! ማዳንና ክብር ኀይልም የአምላካችን ነው! #19፥1 “ሃሌ ሉያ”፦ ማለት በዕብራይስጥ “እግዚአብሔር ይመስገን” ማለት ነው። 2ፍርዱ እውነትና ትክክል ነው፤ ምድርን በአመንዝራነትዋ ያረከሰችውን ታላቂቱን አመንዝራ በፍርድ ቀጥቶአታል፤ እርስዋን በመቅጣትም የአገልጋዮቹን ደም ተበቅሎአል።” #ዘዳ. 32፥43፤ 2ነገ. 9፥7። 3እንደገናም፥ “ሃሌ ሉያ! ከእርስዋ የሚነሣው ጢስ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ወደ ላይ ይወጣል!” እያሉ ጮኹ። #ኢሳ. 34፥10። 4ኻያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ በግንባራቸው ተደፍተው “አሜን፥ ሃሌ ሉያ!” እያሉ ሰገዱ።
የበጉ ሠርግ ግብዣ
5ከዚህ በኋላ “እርሱን የምትፈሩ አገልጋዮቹ ሁሉ፥ ታናናሾችም ታላላቆችም አምላካችንን አመስግኑ!” የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ። #መዝ. 115፥13። 6የብዙ ሰዎችን ድምፅ የወራጅ ውሃን ድምፅ፥ የብርቱ ነጐድጓድንም ድምፅ፥ የሚመስል ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚችል ጌታ አምላካችን ይነግሣል! #ሕዝ. 1፥24፤ መዝ. 93፥1፤ 97፥1፤ 99፥1። 7የበጉ ሠርግ ስለ ደረሰና የእርሱም ሙሽራ ስለ ተዘጋጀች ኑ ደስ ይበለን! ደስታም እናድርግ! እናክብረውም! 8የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ውብ ልብስ እንድትለብስ ተሰጣት፤ ቀጭኑ ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው።”
9ከዚህ በኋላ መልአኩ “ወደ በጉ ሠርግ ግብዣ የተጠሩ የተባረኩ ናቸው” ብለህ ጻፍ አለኝ፤ ቀጥሎም “ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው” አለ። #ማቴ. 22፥2-3።
10እኔም ለመልአኩ ልሰግድለት በእግሩ ሥር በግንባሬ ተደፋሁ፤ እርሱ ግን “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክርነት ከያዙት ወንድሞችህ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ! የኢየሱስ ምስክርነት የትንቢት መንፈስ ነው” አለኝ።
በነጩ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ፈረሰኛ
11ከዚህ በኋላ ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ፥ ነጭ ፈረስም አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ታማኝና እውነተኛ የሚባል ነው፤ እርሱ በትክክል ይፈርዳል፤ ይዋጋልም፤ #ሕዝ. 1፥1፤ መዝ. 96፥13፤ ኢሳ. 11፥4። 12ዐይኖቹ የእሳት ነበልባል ይመስላሉ፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ፤ ከእርሱ በቀር ሌላ ማንም የማያውቀው በእርሱ ላይ የተጻፈ ስም ነበረ፤ #ዳን. 10፥6። 13እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሶ ነበር፤ ስሙም “የእግዚአብሔር ቃል” የሚባል ነው። 14በነጫጭ ፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ነጭና ንጹሕ የሆነ ውብ ልብስ የለበሱ የሰማይ ሠራዊት ተከትለውታል፤ 15ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ በብረት በትርም ይገዛቸዋል፤ እርሱ ሁሉን የሚችለውን የእግዚአብሔር አስፈሪ ቊጣ መግለጫ የሆነውን የወይን ጠጅ መጭመቂያ ይረግጣል፤ #መዝ. 2፥9፤ ኢሳ. 63፥3፤ ኢዮብ 3፥13፤ ራዕ. 14፥20። 16በልብሱና በጭኑ ላይ “የነገሥታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ” የሚል ስም ተጽፎአል።
17ከዚህ በኋላ በፀሐይ ላይ የቆመ አንድ መልአክ አየሁ፤ እርሱ በሰማይ ለሚበርሩ ወፎች እንዲህ ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ “ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር ግብዣ ኑ! ተሰብሰቡ! 18የነገሥታትን ሥጋ፥ የጦር አዛዦችን ሥጋ፥ የብርቱ ጦረኞችን ሥጋ፥ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ፥ የጌቶችንና የአገልጋዮችን ሥጋ፥ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ፥ የማንኛውንም ሰው ሁሉ ሥጋ ኑ ብሉ!”
19እንዲሁም አውሬውና የምድር ነገሥታት፥ ወታደሮቻቸውም በነጩ ፈረስ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ፤ 20ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ ብዙ ተአምራት ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ፤ እርሱ የአውሬው ምልክት የነበረባቸውንና ለአውሬውም ምስል ይሰግዱ የነበሩትን ተአምራት እያደረገ ያስታቸው ነበር፤ እነዚህ ሁለቱ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ከነሕይወታቸው ተጣሉ። #ራዕ. 13፥1-18። 21የቀሩት ደግሞ በነጩ ፈረስ ላይ ከተቀመጠው አፍ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ሥጋቸውን በመብላት ጠገቡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ