የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 18:17-24

የዮሐንስ ራእይ 18:17-24 አማ05

ያን ያኽል ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፋ!” ይላሉ። የመርከብ አዛዦች ሁሉ፥ በመርከብ የሚጓዙ ሰዎች ሁሉ፥ በመርከብ ላይ የሚሠሩ ሁሉ፥ በባሕር ላይ የሚነግዱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ፤ እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ባዩ ጊዜ “ይህችን ታላቅ ከተማ የሚመስል ከቶ ሌላ ከተማ ነበረን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸው ላይ አቧራ ነሰነሱ፤ እያለቀሱና እያዘኑም እንዲህ እያሉ ይጮኻሉ፤ “በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ በእርስዋ ሀብት ሀብታሞች የሆኑ፥ ያቺ ታላቅ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ ወደመች ወዮላት! ወዮላት!” ሰማይ ሆይ! በእርስዋ ደስ ይበልህ! እግዚአብሔር ስለ እናንተ በእርስዋ ላይ ስለ ፈረደባት እናንተ ቅዱሳንና ሐዋርያት ነቢያትም ደስ ይበላችሁ! ከዚህ በኋላ አንድ ብርቱ መልአክ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚያኽል አንድ ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው፤ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ በኀይል ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አትገኝም፤ የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፥ የዋሽንት ነፊዎችና የእምቢልታ ነፊዎች ድምፅ፥ ዳግመኛ በአንቺ አይሰማም፤ ማንኛውንም ዐይነት የእጅ ጥበብ የሚሠራ ብልኀተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አይገኝም፤ የወፍጮም ድምፅ ከእንግዲህ በአንቺ አይሰማም። የመብራት ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አያበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራይቱ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ በአስማትሽ ሕዝቦችን ሁሉ አሳስተሻል። “በእርስዋ ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፥ በምድር ላይ የተገደሉ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቶአል።”