የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 18

18
የባቢሎን መውደቅ
1ከዚህ በኋላ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩ ነጸብራቅ የተነሣ ምድር በራች፤ 2ከፍ ባለ ድምፅም እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ ሆነች! የርኩሳን መናፍስት ማደሪያ ሆነች! የሚያጸይፉና የሚያስጠሉ ወፎች መጠለያ ሆነች! #ኢሳ. 13፥21፤ 21፥9፤ ኤር. 50፥39፤ 51፥8፤ ራዕ. 14፥8። 3የሚያሰክረውን የአመንዝራነትዋን ወይን ጠጅ ለሕዝቦች ሁሉ አጠጥታለች፤ የምድር ነገሥታት ከእርስዋ ጋር አመንዝረዋል፤ የምድር ነጋዴዎችም ከብዙ ምቾትዋ የተነሣ ሀብታሞች ሆነዋል።” #ኢሳ. 23፥17፤ ኤር. 51፥7።
4ሌላ ድምፅም ከሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
“ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ፤
የመቅሠፍትዋም ተካፋዮች እንዳትሆኑ፤
ከእርስዋ ውጡ! #ኢሳ. 48፥20፤ ኤር. 50፥8፤ 51፥6፤45።
5የኃጢአትዋ ክምር እስከ ሰማይ ደርሶአል፤
እግዚአብሔር በደሎችዋን አስታውሶአል፤ #ዘፍ. 18፥20-21፤ ኤር. 51፥9።
6በሰጠችው መጠን ስጥዋት፤
ባደረገችውም ሥራ እጥፍ ክፈልዋት፤
እርስዋ ልዩ ልዩ መጠጦችን በቀላቀለችበት ጽዋ ውስጥ
እጥፍ ኀይለኛ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ #መዝ. 137፥8፤ ኤር. 50፥29።
7እርስዋ ለራስዋ ክብርንና ምቾትን የሰጠችውን ያኽል
ሥቃይና ሐዘን ስጡአት፤
እርስዋ በልብዋ
‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤
መበለትም አይደለሁም፤
ሐዘንም ከቶ አይደርስብኝም’ በማለት ትመካለች።
8ስለዚህ መቅሠፍቶችዋ ሁሉ በአንድ ቀን ይደርሱባታል፤
ሞትና ሐዘን ራብም ይደርሱባታል፤
በእሳትም ትቃጠላለች፤
በእርስዋ ላይ የሚፈርድባት
ጌታ አምላክ ብርቱ ነው።”
9ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ 10ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ አንቺ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ሆይ! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ መጣ፥ ወዮልሽ! ወዮልሽ!” ይላሉ። #ሕዝ. 26፥16-17።
11የመርከባቸውን ጭነት ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ የምድር ነጋዴዎችም ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላታልም፤ #ሕዝ. 27፥31-36። 12በመርከባቸው የተጫነውም ወርቅ፥ ብር፥ የከበረ ድንጋይ፥ ዕንቊ፥ ቀጭን ልብስ፥ ሐምራዊ ልብስ፥ ሐር ልብስ፥ ቀይ ልብስና መልካም መዓዛ ያለው እንጨት ሁሉ፥ ከዝኆን ጥርስ፥ ውድ ከሆነ እንጨት፥ ከነሐስ፥ ከብረትና ከእብነበረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ 13ቀረፋ፥ ቅመም፥ የሚሸት እንጨት፥ ከርቤ፥ ዕጣን፥ ወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ ዱቄት፥ ስንዴ፥ ከብቶች፥ በጎች፥ ፈረሶች፥ ሠረገላዎች፥ ባርያዎችና ሌሎችም ሰዎች ናቸው። #ሕዝ. 27፥12፤ 13፥22። 14ነጋዴዎቹም “አንቺ የተመኘሻቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ከአንቺ ርቀው ሄደዋል፤ ሀብትሽም ጌጣ ጌጥሽም ሁሉ ጠፍቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ እነዚህን ሁሉ ከቶ አታገኚአቸውም!” ይሉአታል። 15እነዚህን ነገሮች ሁሉ እየገዙ ሀብታሞች የሆኑ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ይቆማሉ፤ እያለቀሱና እያዘኑም፥ #ሕዝ. 27፥31፤36። 16“ቀጭን ልብስና ሐምራዊ ልብስ ቀይ ልብስም ትለብስ የነበረች፥ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቊም ታሸበርቅ የነበረች፤ ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! 17ያን ያኽል ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፋ!” ይላሉ።
የመርከብ አዛዦች ሁሉ፥ በመርከብ የሚጓዙ ሰዎች ሁሉ፥ በመርከብ ላይ የሚሠሩ ሁሉ፥ በባሕር ላይ የሚነግዱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ፤ #ኢሳ. 23፥14፤ ሕዝ. 27፥26-30። 18እርስዋ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ባዩ ጊዜ “ይህችን ታላቅ ከተማ የሚመስል ከቶ ሌላ ከተማ ነበረን?” እያሉ ጮኹ። #ሕዝ. 27፥32። 19በራሳቸው ላይ አቧራ ነሰነሱ፤ እያለቀሱና እያዘኑም እንዲህ እያሉ ይጮኻሉ፤ “በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ በእርስዋ ሀብት ሀብታሞች የሆኑ፥ ያቺ ታላቅ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስለ ወደመች ወዮላት! ወዮላት!” #ሕዝ. 27፥30-34።
20ሰማይ ሆይ! በእርስዋ ደስ ይበልህ! እግዚአብሔር ስለ እናንተ በእርስዋ ላይ ስለ ፈረደባት እናንተ ቅዱሳንና ሐዋርያት ነቢያትም ደስ ይበላችሁ! #ዘዳ. 32፥43፤ ኤር. 51፥48።
21ከዚህ በኋላ አንድ ብርቱ መልአክ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚያኽል አንድ ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው፤ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ በኀይል ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አትገኝም፤ #ኤር. 51፥63-64፤ ሕዝ. 26፥21። 22የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፥ የዋሽንት ነፊዎችና የእምቢልታ ነፊዎች ድምፅ፥ ዳግመኛ በአንቺ አይሰማም፤ ማንኛውንም ዐይነት የእጅ ጥበብ የሚሠራ ብልኀተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አይገኝም፤ የወፍጮም ድምፅ ከእንግዲህ በአንቺ አይሰማም። #ሕዝ. 26፥13፤ ኢሳ. 24፥8። 23የመብራት ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አያበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራይቱ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ በአስማትሽ ሕዝቦችን ሁሉ አሳስተሻል። #ኤር. 7፥34፤ 25፥10።
24“በእርስዋ ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፥ በምድር ላይ የተገደሉ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቶአል።” #ኤር. 51፥49።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ