የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 14:1-20

የዮሐንስ ራእይ 14:1-20 አማ05

ከዚህ በኋላ እነሆ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ አየሁ፤ ከእርሱ ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግንባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች ነበሩ። ከሰማይም የታላቅ ፏፏቴ ውሃ ድምፅና ታላቅ ነጐድጓድ የመሰለ ከፍተኛ ድምፅ ሰማሁ፤ የሰማሁትም ድምፅ በገና ደርዳሪዎች በገና እየደረደሩ የሚያሰሙትን ድምፅ ይመስል ነበር። በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች፥ በሽማግሌዎችም ፊት መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ ይህን መዝሙር ከምድር ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች በቀር ማንም ሊማረው አልቻለም። እነርሱ ድንግሎች ስለ ሆኑ ከሴቶች ጋር ግንኙነት በማድረግ አልረከሱም፤ በጉ ወደሚሄድበትም ሁሉ ይከተሉታል። እነርሱ ለእግዚአብሔርና ለበጉ ከሰዎች መካከል እንደ በኲራት የቀረቡ ናቸው። እነርሱ ሐሰት ተናግረው አያውቁም፤ ነቀፋም የሌለባቸው ናቸው። ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ፥ ነገድ፥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩና ለተለያዩ ወገኖች ሁሉ ለማብሠር ዘለዓለማዊውን ወንጌል የያዘ ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ። በታላቅ ድምፅም “እግዚአብሔርን ፍሩ! አክብሩትም! የእርሱ የፍርድ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረ አምላክ ስገዱ!” አለ። ሌላም ሁለተኛው መልአክ “የሚያሰክረውን የዝሙትዋን ወይን ጠጅ ለሕዝቦች ሁሉ ያጠጣች ያቺ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!” እያለ የመጀመሪያውን መልአክ ተከተለ። ሌላ ሦስተኛ መልአክም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው፤ “ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ፥ ምልክቱን በግንባራቸው ወይም በእጃቸው የሚያደርጉ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን የቊጣ የወይን ጠጅ ይጠጣሉ፤ ይህም የወይን ጠጅ ሳይበረዝ በቊጣው ጽዋ የተቀዳ ነው፤ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክት ፊትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሠቃያሉ፤ እነርሱን ከሚያሠቃየው እሳት የሚወጣው ጢስ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ወደ ላይ ይወጣል፤ ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት ያደረጉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።” የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ከሚጠብቁና ኢየሱስንም በማመን ከሚጸኑ ቅዱሳን የሚጠበቀው ትዕግሥት እዚህ ላይ ነው። ከሰማይም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፤ ይህን ጻፍ፤ “ከእንግዲህ ወዲህ የጌታ ኢየሱስ ሆነው የሚሞቱ የተባረኩ ናቸው!” መንፈስ ቅዱስም “አዎ! ከድካማቸው እንዲያርፉ ሥራቸው ይከተላቸዋል” ይላል። ከዚህ በኋላ ተመለከትኩ፤ እነሆ፥ ነጭ ደመና አየሁ፤ በደመናው ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፤ በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል አድርጎአል፤ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዞአል፤ ሌላ መልአክ ከመቅደሱ ወጣና በደመና ላይ የተቀመጠውን ከፍ ባለ ድምፅ “የምድር መከር ደርሶአል! የዐጨዳ ሰዓትም ቀርቦአል!” በደመናው ላይ የተቀመጠውም ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ ምድርም ታጨደች። ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም ስለታም ማጭድ ይዞ ነበር። በእሳት ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው አጠገብ ወጣና ስለታም ማጭድ የያዘውን መልአክ “የዘለላዎቹ ፍሬዎች ስለ በሰሉ ስለታም ማጭድህን ስደድ! የወይን ዘለላዎችን ሁሉ ከምድር ወይን ቈርጠህ ሰብስብ!” በማለት ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ። መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደው፤ የምድርንም ወይን ዘለላ ቈረጠ፤ በታላቁም የእግዚአብሔር ቊጣ መጭመቂያ ውስጥ ጣለው። ከከተማው ውጪ ባለው በወይን መጭመቂያም ተጨመቀ፤ ከመጭመቂያውም እስከ ፈረስ ልጓም ወደ ላይ ከፍ ያለና ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚደርስ ደም ወጥቶ ፈሰሰ።