የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 86

86
ከእግዚአብሔር ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ! ችግረኛና ድኻ ስለ ሆንኩ
እባክህ ጸሎቴን ስማ፤ መልስም ስጠኝ።
2እኔ ለአንተ ታማኝ ስለ ሆንኩ ሕይወቴን ጠብቃት፤
አንተ አምላኬ ነህ፤ በአንተ የምታምነውን እኔን አገልጋይህን አድነኝ።
3ጌታዬ ሆይ! ማረኝ፤
ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጸልያለሁ።
4አምላክ ሆይ!
ጸሎቴን ወደ ላይ ወደ አንተ ስለማሰማ
እኔን አገልጋይህን ደስ አሰኘኝ።
5ጌታ ሆይ! አንተ ለእኛ ቸርና መሐሪ ነህ፤
ወደ አንተ ለሚጸልዩትም ሁሉ
ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ታሳያቸዋለህ።
6እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ፤
የልመናዬንም ጩኸት አድምጥ።
7አንተ ለጸሎቴ መልስ ስለምትሰጥ
በመከራ ጊዜ ወደ አንተ እጮኻለሁ።
8ጌታ ሆይ! ከአማልክት መካከል አንተን የሚመስል የለም፤
አንተ ያደረግኸውን ያደረገ ማንም የለም።
9አንተ የፈጠርካቸው ሕዝቦች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ፤
ለአንተም ይሰግዳሉ፤
የአንተንም ስም ያከብራሉ። #ራዕ. 15፥4።
10አንተ ታላቅ ስለ ሆንክና አስደናቂ ድርጊቶችንም ስለምታደርግ
አምላክ አንተ ብቻ ነህ።
11እግዚአብሔር ሆይ!
የእውነት መንገድህን እከተል ዘንድ አስተምረኝ፤
ባልተከፋፈለ ልብም እንዳከብርህ አድርገኝ።
12ጌታ አምላኬ ሆይ! በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፤
ስምህንም ለዘለዓለም አከብራለሁ።
13ለእኔ የምታሳየው ዘለዓለማዊው ፍቅርህ እንዴት
ታላቅ ነው!
ወደ ሲኦል ጥልቀት ከመውረድ አዳንከኝ።
14አምላክ ሆይ! ትዕቢተኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፤
አንተን የማይፈሩ ጨካኞች ሰዎች ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ።
15እግዚአብሔር ሆይ!
አንተ ግን መሐሪና ርኅሩኅ ለቊጣ የዘገየህ፥
የተትረፈረፈ ፍቅርና ታማኝነት ያለህ አምላክ ነህ።
16ወደ እኔ ተመልሰህ ራራልኝ፤
ለእኔ ለአገልጋይህ ብርታትን ስጠኝ፤
እኔን የሴት አገልጋይህን ልጅ አድነኝ።
17እግዚአብሔር ሆይ!
አንተ ስለ ረዳኸኝና ስላጽናናኸኝ፥
ጠላቶቼ አይተው ያፍሩ ዘንድ፥
ለእኔ ሞገስን የመስጠት ምልክትህን አሳየኝ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ