መጽሐፈ መዝሙር 36:1-12

መጽሐፈ መዝሙር 36:1-12 አማ05

ክፉ ሰው ሁልጊዜ በልቡ ክፋትን ያስባል፤ እግዚአብሔርን ከቶ አይፈራም፤ አያከብረውምም። ክፉ ሰው ክፋቱ ስለሚያቈላምጠው ኃጢአቱን ለማየትም ሆነ ለመጥላት አይፈልግም። ንግግሩ ተንኰልንና ሐሰትን የተሞላ ነው፤ መልካም ሥነ ምግባርን ሁሉ መረዳት አቃተው። በመኝታውም ላይ ሳለ ተንኰልን ያቅዳል፤ ራሱን ወደ ክፉ መንገድ ይመራል። ክፉውን ነገር አያስወግድም። እግዚአብሔር ሆይ፥ ዘለዓለማዊ ፍቅርህ እስከ ሰማይ፥ እውነተኛነትህም እስከ ደመና ይደርሳል። እግዚአብሔር ሆይ፥ ሰዎችንና እንስሶችን ከአደጋ ታድናለህ፤ ጽድቅህ እንደ ተራራዎች እጅግ ከፍ ያለ ነው፤ ፍርድህም እንደ ባሕር ጥልቅ ነው። አምላክ ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ምንኛ ክቡር ነው! ሰዎች በአንተ ጥበቃ ሥር ይከለላሉ። በቤትህ የተትረፈረፈውን ምግብ ይጋበዛሉ፤ አስደሳች ከሆነ ወንዝህም ታጠጣቸዋለህ። አንተ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነህ፤ ከአንተም ብርሃን የተነሣ ብርሃን እናያለን፤ ለሚያውቁህ ዘለዓለማዊ ፍቅርህ አይቋረጥባቸው፤ አዳኝነትህም ለልበ ቅኖች ይቀጥል። የትዕቢተኞች እግር እንዲረግጠኝ፥ የክፉዎች እጅ እንዲአባርረኝ አታድርግ። ክፉዎች እንዴት እንደ ወደቁ እይ። እነሆ ተጥለዋል፤ መነሣትም አይችሉም።