መዝሙር 36:1-12

መዝሙር 36:1-12 NASV

ክፉውን ሰው፣ በደል በልቡ ታናግረዋለች፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር፣ በዐይኖቹ ፊት የለም። በደሉ ግልጽ ወጥቶ እንዳይጠላ፣ ራሱን በራሱ እጅግ ይሸነግላልና። ከአንደበቱ የሚወጣው የክፋትና የተንኰል ቃል ነው፤ ማስተዋልንና በጎ ማድረግን ትቷል። በመኝታው ላይ ክፋትን ያውጠነጥናል፤ ራሱን በጎ ባልሆነ መንገድ ይመራል፤ ክፋትንም አያርቅም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ እስከ ሰማያት ይደርሳል፤ ታማኝነትህም እስከ ጠፈር ይመጥቃል። ጽድቅህ እንደ ታላላቅ ተራሮች፣ ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰውንም እንስሳንም ታድናለህ። አምላክ ሆይ፤ ምሕረትህ እንዴት ክቡር ነው! የሰዎች ልጆች ሁሉ፣ በክንፎችህ ጥላ ሥር መጠጊያ ያገኛሉ። ከቤትህ ሲሳይ ይመገባሉ፤ ከበረከትህም ወንዝ ይጠጣሉ። የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፣ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን። ለሚያውቁህ ምሕረትህ፣ ልባቸውም ለቀና ጽድቅህ ዘወትር አይቋረጥባቸው። የትዕቢተኛ እግር በላዬ አይምጣ፤ የክፉውም ሰው እጅ አያሳድደኝ። ክፉ አድራጊዎች እንዴት እንደ ወደቁና እንደ ተጋደሙ፣ ቍልቍልም እንደ ተወረወሩና መነሣት እንደማይችሉ ተመልከት!