መጽሐፈ መዝሙር 35:17-28

መጽሐፈ መዝሙር 35:17-28 አማ05

እግዚአብሔር ሆይ! እስከ መቼ ድረስ ዝም ብለህ ታየኛለህ? ከክፉ ሥራቸው አድነኝ፤ ከእነዚህ እንደ አንበሳ ጨካኝ ከሆኑ ሰዎች ታደገኝ! በዚያን ጊዜ በሕዝብ ጉባኤ መካከል ሆኜ አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበበት ቦታ አከብርሃለሁ። ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ጠላቶቼ በእኔ ምክንያት እንዲደሰቱ አታድርግ፤ በኋላዬ ሆነው እንዲጠቃቀሱብኝም አታድርግ። አነጋገራቸው የጠላት አነጋገር ነው፤ በሰላማዊ ሰው ላይ ተንኰልን ያቅዳሉ። “ይኸዋ! ይኸዋ! እኛ ራሳችን የሠራኸውን አየን!” እያሉ በመጮኽ ያሳጡኛል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህን ተመልክተሃል፤ ስለዚህ ጌታ ሆይ! ዝም አትበል! ከእኔም አትራቅ! ጌታዬና አምላኬ ሆይ! ተነሥተህ ተከላከልልኝ፤ ተነሥተህም ፍረድልኝ። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እንደ ጻድቅነትህ በእውነት ፍረድልኝ፤ ጠላቶቼም በእኔ ላይ ደስ እንዲላቸው አታድርግ። “ይኸዋ የልባችን ምኞት ደረሰ!” ብለው እንዲያስቡና ወይም “እኛ አሸነፍነው!” እንዲሉ አታድርግ። በእኔ መከራ ተደስተው ትኲር ብለው በንቀት የሚመለከቱኝ ሁሉ ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፤ በእኔ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ሁሉ ኀፍረትንና ውርደትን ይልበሱ። ድል ማድረጌ የሚያስደስታቸው ሁሉ ደስ ይበላቸው፤ “እግዚአብሔር ታላቅ ነው! ለአገልጋዩ ሁኔታዎች ሁሉ ሲሳኩለት እግዚአብሔር ደስ ይለዋል!” ይበሉ። አንደበቴ ቀኑን ሙሉ ስለ ጽድቅህና ስለ ምስጋናህ ይናገራል።