የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 22:1-31

መጽሐፈ መዝሙር 22:1-31 አማ05

አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ? እኔን ከማዳን የራቅኸው ለምንድን ነው? ከመቃተት ድምፄስ የራቅኸው ለምንድን ነው? አምላኬ ሆይ! በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አንተ ግን አትሰማኝም፤ በሌሊት እጣራለሁ፤ ዕረፍትም የለኝም። ሆኖም አንተ በእስራኤል የተመሰገንክ፥ በዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ የምትገዛ ቅዱስ አምላክ ነህ። የቀድሞ አባቶቻችን በአንተ ተማመኑ፤ በአንተም ስለ ተማመኑ አዳንካቸው። ለእርዳታ ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ አዳንካቸው፤ አንተን በተማመኑ ጊዜ አላሳፈርካቸውም። እኔ ግን ከሰው ሁሉ ያነስኩ ትል ነኝ፤ ሰዎች ያፌዙብኛል በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ። የሚያዩኝ ሰዎች ሁሉ ይዘባበቱብኛል፤ ፊታቸውን ያኰሳትሩብኛል፤ ራሳቸውንም ይነቀንቁብኛል። “እግዚአብሔር ያድነው ዘንድ በእርሱ ተማምኖአልና የሚወደው ከሆነ እስቲ ያድነው” ይላሉ። በደኅና እንድወለድ ያደረግኸኝ አንተ ነህ፤ የእናቴን ጡት በምጠባበት በሕፃንነቴ ወራት እንኳ የጠበቅኸኝ አንተ ነህ። ከተወለድኩበት ቀን ጀምሮ በአንተ ጥበቃ ሥር ነኝ፤ ከልደቴ ጊዜም ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ። መከራ ሊደርስብኝ ስለ ተቃረበና የሚረዳኝም ስለሌለ እባክህ ከእኔ አትራቅ! ብዙ ጠላቶች እንደሚዋጉ በሬዎች ከበውኛል፤ እንደ ባሳን ተዋጊ ኰርማዎችም በዙሪያዬ ናቸው፤ የሚበላውን ነገር አድኖ ለመቦጫጨቅ እንደሚያገሣ አንበሳ ጠላቶቼ አፋቸውን ከፈቱብኝ። ጒልበቴ ደክሞ እንደ ውሃ ፈሰሰ፤ አጥንቶቼ ሁሉ ከመገጣጠሚያቸው ተለያዩ፤ ልቤም እንደ ሰም በውስጤ ቀለጠ። ጒሮሮዬ እንደ ሸክላ ደረቀ፤ ምላሴም ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ፤ እንደ ሞተ ሰው በትቢያ ላይ ተውከኝ። ክፉ ሰዎች እንደ ውሻ ስብስብ ከበቡኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩ። አጥንቶቼ ተቈጠሩ፤ ጠላቶቼም አተኲረው እያዩ በማፌዝ ተመለከቱኝ። ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። እግዚአብሔር ሆይ! ከእኔ አትራቅ፤ ረዳቴ ሆይ! እኔን ለመርዳት ፈጥነህ ድረስ። ነፍሴን ከሰይፍና ከእነዚያ ውሾች ኀይል አድነኝ። ከአንበሳ አፍ አድነኝ ከተዋጊ ጐሽ ቀንድም ጠብቀኝ። የስምህን ታላቅነት ለወገኖቼ እናገራለሁ፤ እነርሱ በተሰበሰቡበት ስፍራ አመሰግንሃለሁ፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩት አመስግኑት! እናንተ የያዕቆብ ዘሮች ሁሉ አክብሩት! እናንተ የእስራኤል ዘሮች ሁሉ በፍርሃት ከፍ ከፍ አድርጉት! የተጨቈነውን ሰው አልናቀውም፤ በሁናቴውም አልተጸየፈውም፤ ፊቱን ከእርሱ አልሰወረም፤ ነገር ግን ለእርዳታ የሚያደርገውን ጩኸት አዳመጠው። ስለ ሠራኸው መልካም ሥራ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ አመሰግንሃለሁ፤ በሚፈሩህ ሰዎች ፊት ሆኜ፥ የተሳልኩትን ስለት እፈጽማለሁ። ድኾች እስኪጠግቡ ይበላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹት ያመሰግኑታል፤ ልባቸው በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ይደሰታል። እስከ ምድር ዳርቻ ያሉ ሰዎች ሁሉ አስታውሰው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ በዓለም የሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ። ሥልጣን ሁሉ የአንተ ነው፤ ሕዝቦችም ሁሉ ይገዙልሃል። ጌታ ሆይ! የተትረፈረፈ ሀብት ያላቸው ሁሉ ይሰግዱልሃል። ለሞትና ለመቃብር የተቃረቡትም መጥተው ይንበረከኩልሃል። መጪው ትውልድ ያገለግለዋል፤ የወደፊት ትውልድም ስለ እግዚአብሔር ይነገረዋል። እነርሱ የጽድቅ ሥራውን በማወጅ “እግዚአብሔር ሕዝቡን አዳነ” ብለው ገና ላልተወለዱ ሰዎች ይናገራሉ።