የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 145

145
የምስጋና መዝሙር
1አምላኬና ንጉሤ ሆይ!
ታላቅነትህን ዐውጃለሁ፤
ለዘለዓለምም አመሰግንሃለሁ።
2በየቀኑ አመሰግንሃለሁ፤
ለዘለዓለምም ስምህን አከብራለሁ።
3እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤
ከፍተኛ ምስጋናም የሚገባው ነው፤
ታላቅነቱም ሰው ከሚያስተውለው በላይ ነው።
4አንድ ትውልድ የአንተን ሥራ ለሚቀጥለው ትውልድ
ያስተላልፋል፤ ድንቅ ሥራህንም ይገልጣል።
5ሕዝቦች ስለ ክብርህና ስለ ግርማህ ታላቅነት ያወራሉ፤
እኔም ድንቅ ስለ ሆነው ሥራህ አሰላስላለሁ።
6ሕዝቦች አስደናቂ ስለ ሆኑት ታላላቅ ሥራዎችህ ይናገራሉ፤
እኔም ታላቅነትህን ዐውጃለሁ።
7ስለ ደግነትህ ገናናነት ይናገራሉ፤
ስለ ጽድቅህ ኀይል ከፍ ባለ ድምፅ ይዘምራሉ።
8እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው፤
ለቊጣ የዘገየና በዘለዓለማዊ ፍቅር የተሞላ ነው።
9እርሱ ለሰው ሁሉ ቸር ነው፤
ለፍጡሮቹም ሁሉ ይራራል።
10እግዚአብሔር ሆይ!
ፍጡሮችህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፤
ሕዝቦችህም ሁሉ ያወድሱሃል።
11ስለ ንጉሥነትህ ክብር ያወራሉ፤
ስለ ኀይልህም ይናገራሉ።
12በዚህ ዐይነት ሰዎች ሁሉ
በኀይልህ ስላደረግሃቸው ታላላቅ ሥራዎችና
ስለ መንግሥትህም ታላቅ ግርማ ያውቃሉ።
13ግዛትህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል።
መንግሥትህም ዘለዓለማዊ ነው።
እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ የታመነ ነው፤
እርሱ የሚያደርገው ሁሉ መልካም ነው።
14የሚንገዳገዱትን ይደግፋል፤
የወደቁትንም ያነሣቸዋል።
15ሁሉም በተስፋ ወደ አንተ ይመለከታሉ፤
አንተም በሚያስፈልጋቸው ጊዜ
ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ።
16እጅህን ከፍተህ
የእያንዳንዱን ሕያው ፍጥረት ፍላጎት ታረካለህ።
17እግዚአብሔር በሚያደርገው ሁሉ እውነተኛ ነው፤
በሥራውም ሁሉ ታማኝ ነው።
18እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥
ማለትም በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።
19በአክብሮት ለሚፈሩት
የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ይሰጣቸዋል፤
ጩኸታቸውንም ሰምቶ ያድናቸዋል።
20እርሱን የሚወዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤
ክፉዎችን ግን ይደመስሳል።
21እኔ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤
እርሱ የፈጠራቸው ሁሉ
ቅዱስ ስሙን ለዘለዓለም ያወድሱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ