መጽሐፈ መዝሙር 144
144
የድል አድራጊነት መዝሙር
1መጠጊያዬ እግዚአብሔር ይመስገን!
ለሰልፍ ያሠለጥነኛል፤ ለጦርነትም ያዘጋጀኛል።
2እግዚአብሔር ጠባቂዬና መከታዬ ነው፤
መጠለያዬና አዳኜ ነው፤
በእርሱ ተማምኜ በሰላም እኖራለሁ፤
እርሱ አሕዛብን ከእግሬ በታች አድርጎ ያስገዛልኛል።
3እግዚአብሔር ሆይ!
ይህን ያኽል የምትንከባከበው ሰው ምንድን ነው?
ይህን ያኽልስ የምታስብለት የሰው ልጅ ምንድን ነው? #ኢዮብ 7፥17-18፤ መዝ. 8፥4።
4ሰው እንደ ነፋስ ሽውታ ነው፤
ዘመኑም እንደ ጥላ የሚያልፍ ነው።
5እግዚአብሔር ሆይ! ሰማይን ሰንጥቀህ ውረድ፤
ተራራዎችን ዳስስ፤ እነርሱም ይጢሱ።
6የመብረቅ ብልጭታን ልከህ ጠላቶችህን በትናቸው፤
ፍላጻዎችህንም በመወርወር አሳዳቸው።
7እጅህን ከላይ ስደድ፤
ከጥልቅ ውሃ ውስጥ ስበህ አውጣኝ፤ ታደገኝም፤
ከባዕዳን ኀይል አድነኝ።
8እነርሱ ከቶ እውነት አይናገሩም፤
ቀኝ እጃቸውን አንሥተው የሚምሉት በሐሰት ነው።
9አምላክ ሆይ! አዲስ መዝሙር እቀኝልሃለሁ፤
ዐሥር አውታር ያለው በገናም በመደርደር እዘምርልሃለሁ።
10አንተ ለነገሥታት ድልን ታጐናጽፋለህ፤
አገልጋይህን ዳዊትንም ከስለታም ሰይፍ ትታደገዋለህ።
11ከባዕዳን ጠላቶች እጅ ታድገህ አድነኝ፤
አፋቸው ሐሰትን ይናገራል፤
ቀኝ እጃቸውም ለሐሰት መሐላ ይነሣል።
12ወንዶች ልጆቻችን በወጣትነታቸው ጊዜ
እንደ አዲስ ተክል የሚያድጉና የሚጠነክሩ ይሁኑ፤
ሴቶች ልጆቻችን ለቤተ መንግሥት ማእዘኖች
ውበት እንደሚሰጡ፥ ተቀርጸው ቀጥ
እንዳሉ ምሰሶች ይሁኑ።
13ጐተራዎቻችን በልዩ ልዩ ዐይነት እህል የተሞሉ ይሁኑ፤
በመስኮቻችን ላይ የተሰማሩት በጎች
በሺህ የሚቈጠሩ ግልገሎችን እየወለዱ ይብዙ።
14ከብቶቻችን የሰቡ ይሁኑ፤
ሳይጨነግፉም በመርባት ይብዙ፤
በመንገዶቻችን የሐዘን ጩኸት ከቶ አይሰማ።
15እንደዚህ የሚሆንለት ሕዝብ የተባረከ ነው!
እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ የተባረከ ነው!
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 144: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997