የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 143

143
የእግዚአብሔርን ዕርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ!
ለምሕረት የማደርገውን ልመና አድምጥ!
በታማኝነትህና በእውነተኛነትህ ለጸሎቴ መልስ ስጠኝ!
2በአንተ ፊት ማንም ጻድቅ ሰው ስለሌለ
እኔን አገልጋይህን ለፍርድ አታቅርበኝ። #ሮም 3፥20፤ ገላ. 2፥16።
3ጠላቴ በማሳደድ ተከታተለኝ፤
በጨለማ ውስጥም አስሮ አጐሳቈለኝ፤
ከብዙ ዘመናት በፊት እንደ ሞቱ ሰዎች ሆኜአለሁ።
4ከዚህም የተነሣ መንፈሴ በውስጤ ዛለብኝ፤
ልቤም ተስፋ ቈረጠ።
5ከብዙ ጊዜ በፊት የነበረውን አስታውሳለሁ፤
ሥራዎችህንም ሁሉ አሰላስላለሁ፤
የእጅህን ሥራዎች ሁሉ አስተውላለሁ።
6እጆቼን ለጸሎት ወደ አንተ እዘረጋለሁ፤
ደረቅ ምድር ውሃ እንደሚያስፈልገው
እንዲሁም ነፍሴ አንተን ተጠማች።
7እግዚአብሔር ሆይ! መንፈሴ ስለ ዛለብኝ
ፈጥነህ መልስ ስጠኝ!
ፊትህን ከእኔ አትሰውርብኝ!
አለበለዚያ ወደ ጥልቁ ጒድጓድ እንደሚወርዱት ሰዎች እሆናለሁ።
8የምተማመነው በአንተ ስለ ሆነ
በየጠዋቱ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳውቅ አድርገኝ፤
ሕይወቴን በዐደራ ለአንተ ስለ ሰጠሁ
የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ።
9እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ስለ ተማጠንኩ
ከጠላቶቼ አድነኝ።
10አንተ አምላኬ ነህ፤
ፈቃድህን እንዳደርግ አስተምረኝ፤
በመልካም ቸርነትህ በደኅና መንገድ ምራኝ።
11እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ክብርህ ሕይወቴን ጠብቅ፤
በእውነተኛነትህም ከችግሬ ሁሉ ነጻ አውጣኝ።
12ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥልኝ፤
ጠላቶቼን አጥፋቸው፤
እኔ አገልጋይህ ስለ ሆንኩ ጥቃት የሚያደርሱብኝን ሁሉ ደምስሳቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ