የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 140

140
የእግዚአብሔርን ጠባቂነት ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ! ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤
ከዐመፀኞች እጅም ጠብቀኝ።
2የእነርሱ ልብ ክፉ ዕቅዶችን ያቅዳል፤
ዘወትርም ጥልን ያነሣሣሉ።
3ምላሳቸው እንደ መርዛም እባብ ተናዳፊ ነው፤
ቃላቸውም እንደ እፉኝት መርዝ ነው። #ሮም 3፥13።
4እግዚአብሔር ሆይ! ከክፉዎች ኀይል ጠብቀኝ፤
እኔን ለመጣል ከሚያቅዱ
ከዐመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ።
5ትምክሕተኞች ወጥመድ ዘረጉብኝ፥
እንደ መረብ የተጠላለፈ ገመድም ዘረጉብኝ።
እኔንም ለመያዝ በመንገዴ ላይ ወጥመድ አጠመዱ።
6እግዚአብሔርን “አንተ አምላኬ ነህ” እለዋለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ! ምሕረትህን ለማግኘት ስጸልይ ስማኝ!
7ኀያሉ አዳኜ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ!
በጦርነት ቀን ራሴን እንደ ጋሻ ሸፍንልኝ።
8ለክፉዎች የሚፈልጉትን ነገር አትስጣቸው፤
ዕቅዳቸው እንዲሰምር አታድርግ።
9የከበቡኝ ጠላቶቼ በእኔ ላይ ያቀዱትን ሤራ
በእነርሱ ላይ እንዲፈጸም አድርግ።
10የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤
ወደ ጒድጓድም ይጣሉ፤
ከዚያም ከቶ አይውጡ።
11ሌሎችን በሐሰት የሚከስሱ በምድር ላይ ጸንተው አይኑሩ፤
ክፉ ነገር በጨካኞች ሰዎች ላይ ይድረስ፤
ይደምስሳቸውም።
12እግዚአብሔር ሆይ! ለድኾች እንደምትፈርድ፥
ለተጨቈኑትም መብታቸውን እንደምታስከብር ዐውቃለሁ።
13ደጋግ ሰዎች በእውነት ያመሰግኑሃል፤
በፊትህም ጸንተው ይኖራሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ