መጽሐፈ መዝሙር 139:1-12

መጽሐፈ መዝሙር 139:1-12 አማ05

እግዚአብሔር ሆይ! መርምረህ ዐውቀኸኛል። አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሣ ታውቃለህ፤ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ ሆነህ ታስተውላለህ። የምጓዝበትንና የማርፍበትን ቦታ ታስተውላለህ፤ ተግባሬን ሁሉ ታውቃለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ገና ከመናገሬ በፊት ምን ለማለት እንደማስብ ታውቃለህ። በዙሪያዬ ሁሉ ትገኛለህ፤ በኀይልህም ትጠብቀኛለህ። የአንተ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ ነው፤ እኔ ላስተውለው ከምችለው በላይ ነው። ከአንተ ለማምለጥ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ከፊትህስ ርቄ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ እዚያ ትገኛለህ፤ ወደ ሙታን ዓለም ብወርድ በዚያም አንተ አለህ። ከፀሐይ መውጫ ባሻገር በርሬ ብሄድ፥ ወይም በፀሐይ መግቢያ በኩል ርቄ ብኖር፥ እዚያ ተገኝተህ በእጅህ ትመራኛለህ፤ በቀኝ እጅህም ትደግፈኛለህ። ጨለማን “ሰውረኝ” ወይም ብርሃንን “ወደ ሌሊት ተለወጥልኝ” ብል ጨለማ እንኳ በአንተ ዘንድ አይጨልምም፤ ሌሊቱም የቀን ያኽል ያበራል፤ ስለዚህ በአንተ ዘንድ ጨለማና ብርሃን ልዩነት የላቸውም።