መጽሐፈ መዝሙር 135
135
የምስጋና መዝሙር
1እግዚአብሔርን አመስግኑ!
እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች፥
ስሙን አመስግኑ!
2በአምላካችን መቅደስ፥ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ
የምትቆሙ ሁሉ አመስግኑት!
3ደግ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ!
ቸር ስለ ሆነ ለስሙ ዘምሩ!
4እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ፥
የእስራኤልንም ሕዝብ የግሉ አድርጎ መረጠ።
5እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ የሚበልጥ
ታላቅ አምላክ መሆኑን ዐውቃለሁ።
6በሰማይና በምድር፥ በጥልቅ ባሕሮችም
የወደደውን ሁሉ ያደርጋል።
7ዝናብ ያዘለ ደመናን ከምድር ዳርቻ ያመጣል፤
በዝናብ ጊዜ መብረቅ እንዲኖር ያደርጋል፤
ነፋስንም ከቦታው ያወጣዋል።
8በግብጽ አገር የሰዎችንና የእንስሶችን
የበኲር ልጆችን የገደለ እርሱ ነው።
9በዚያ ንጉሡን ፈርዖንንና አገልጋዮቹን ሁሉ ለመቅጣት
ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን አደረገ።
10ብዙ የአሕዛብ መንግሥታትን ደመሰሰ፤
ኀያላን ነገሥታትንም ገደለ።
11የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን፥
የባሳንንም ንጉሥ ዖግን፥
የከነዓንንም ነገሥታት ሁሉ ገደለ።
12ምድራቸውንም ለሕዝቡ ለእስራኤል ርስት አድርጎ ሰጠ።
13እግዚአብሔር ሆይ! ስምህ ዘወትር ሲታወጅ ይኖራል፤
ትውልድ ሁሉ ያስታውሱሃል።
14እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፤
ለአገልጋዮቹም ይራራል።
15የአሕዛብ አማልክት
ከብርና ከወርቅ በሰው እጅ የተሠሩ ጣዖቶች ናቸው።
16አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤
ዐይን አላቸው፤ አያዩም።
17ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤
በአፍንጫቸውም መተንፈስ አይችሉም።
18የሠሩአቸውና የሚታመኑባቸው ሁሉ
እንደነዚህ ጣዖቶች ናቸው።
19የእስራኤል ሕዝብ ሆይ!
እግዚአብሔርን አመስግኑ!
እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት
እግዚአብሔርን አመስግኑ!
20እናንተ ሌዋውያን እግዚአብሔርን አመስግኑ!
እግዚአብሔርን የምታከብሩ ሁሉ
እግዚአብሔርን አመስግኑ!
21እግዚአብሔርን በጽዮን አመስግኑት!
በመኖሪያው በኢየሩሳሌም አመስግኑት!
እግዚአብሔርን አመስግኑ!
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 135: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997