መጽሐፈ መዝሙር 109
109
በመከራ ውስጥ ያለ ሰው ሮሮ
1የማመሰግንህ አምላክ ሆይ፥
እባክህ ዝም አትበል።
2ክፉዎችና ሐሰተኞች ተቃውመውኛል፤
በእኔ ላይ በሐሰት ይናገራሉ።
3በጥላቻ ዙሪያዬን ከበቡኝ፤
ያለ ምክንያትም አደጋ ጣሉብኝ
4ለወዳጅነቴ የመለሱልኝ አጸፋ ክስ ነው፤
እኔ ግን እጸልይላቸዋለሁ።
5በመልካም ፈንታ ክፉ፥ በፍቅር ፈንታ ጥላቻ
ይመልሱልኛል።
6በእርሱ ላይ የሚፈርድ ዐመፀኛ ዳኛ ሠይም
አንዱም ሰው እንዲከስሰው አድርግ፤
7በተሟገተ ጊዜ ተረትቶ ይመለስ፤
ጸሎቱ እንኳ እንደ ኃጢአት ይቈጠርበት፤
8ዕድሜውም በቶሎ ይቀጭ፤
ሥራውንም ሌላ ሰው ይውሰድበት። #ሐ.ሥ. 1፥20።
9ልጆቹ ያለ አባት ይቅሩ፤
ሚስቱም ባልዋ የሞተባት ሴት ትሁን።
10ልጆቹ ቤት የሌላቸው ለማኞች ይሁኑ፤
አሁን ከሚኖሩበት ፍርስራሽ ቤት እንኳ ይባረሩ።
11ንብረቱ ሁሉ በዕዳ ይያዝበት፤
ለፍቶ ያገኘውን ጥሪት ሁሉ
ባዕዳን ሰዎች ይውሰዱበት።
12የሚራራለት ሰው ከቶ አይኑር፤
ድኻ ዐደግ ልጆቹን የሚንከባከባቸው ሰው አይገኝ።
13ለስሙ መጠሪያ የሚሆን አንድ ልጅ እንኳ አይቅርለት፤
ከአንድ ትውልድ በኋላ የሚያስታውሰው አይኑር።
14እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶቹን ኃጢአት ያስብበት፤
የእናቱንም ኃጢአት ይቅር አይበልላት።
15እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ዘወትር ያስታውስ፤
እነርሱ ራሳቸው ግን ፈጽሞ የተረሱ ይሁኑ።
16ሰውየው ደግ ሥራ ለማድረግ ፈጽሞ አላሰበም፤
ድኾችን፥ ችግረኞችንና ምስኪኖችን እያሳደደ ይገድል ነበር።
17መራገም ይወድ ስለ ነበር፥ እርሱም የተረገመ ይሁን፤
መመረቅን ይጠላ ስለ ነበር፥ እርሱንም የሚመርቅ
ሰው አይኑር።
18መራገም ልብስ የመልበስ ያኽል ይቀልለው ነበር፤
ስለዚህ የራሱ ርግማን እንደ ውሃ
ወደ ሰውነቱ ገብቶ ያረስርሰው፤
እንደ ዘይትም ወደ አጥንቱ ዘልቆ ይግባ።
19እንደ ልብስ ይሸፍነው፤
እንደ ቀበቶም ዘወትር በወገቡ ዙሪያ ይሁን።
20እግዚአብሔር ሆይ!
ይህን ሁሉ ክፉ ነገር በእኔ ላይ የሚናገሩትን
ጠላቶቼን በዚህ ዐይነት ቅጣቸው።
21ጌታ እግዚአብሔር ሆይ!
ለክብርህ ተገቢ የሆነውን አድርግልኝ፤
ዘለዓለማዊው ፍቅርህም ድንቅ ስለ ሆነ አድነኝ።
22እኔ ድኻና ምስኪን ነኝ፤
የደረሰብኝም መከራ ልቤን አቊስሎታል።
23እንደ ማታ ጥላ ላልፍ ተቃርቤአለሁ፤
እንደ አንበጣም በነፋስ ተወስጄአለሁ።
24ጒልበቶቼ በጾም ደከሙ፤
ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ።
25ጠላቶቼ እኔን በማየት ይስቃሉ፤
በንቀትም ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። #ማቴ. 27፥39፤ ማር. 15፥29።
26እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እባክህ እርዳኝ፤
ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህም አድነኝ።
27የምታድነኝ አንተ ብቻ እንደ ሆንክ
ጠላቶቼ እንዲያውቁ አድርግ።
28እነርሱ ይረግሙኛል፤
አንተ ግን ትመርቀኛለህ፤
አሳዳጆቼን አዋርዳቸው፤
እኔን አገልጋይህን ግን ደስ አሰኘኝ።
29ጠላቶቼ ውርደትን እንደ ልብስ ይልበሱ፤
ኀፍረትንም እንደ መጐናጸፊያ ይደርቡ።
30ድምፄን ከፍ አድርጌ ለእግዚአብሔር ክብር እሰጣለሁ፤
በሕዝብ ጉባኤ መካከል አመሰግነዋለሁ።
31ምክንያቱም እርሱ ሊገድሉት ከተዘጋጁ ሰዎች እጅ ሊያድነው
ስለ ድኻ ሰው መብት ይከራከራል፤
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 109: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997