መጽሐፈ መዝሙር 106
106
እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚያሳየው ቸርነት
1እግዚአብሔርን አመስግኑ!
ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ፥
እግዚአብሔርን አመስግኑ! #1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 107፥1፤ 118፥1፤ 136፥1፤ ኤር. 33፥11።
2እርሱ ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች
ማን ቈጥሮ ሊደርስባቸው ይችላል?
የሚገባውንስ ያኽል ሊያመሰግነው የሚችል ማን ነው?
3ፍትሕን የሚከተሉና
ዘወትር ትክክለኛ የሆነውን ነገር የሚያደርጉ፥
እንዴት የተባረኩ ናቸው?
4እግዚአብሔር ሆይ!
ሕዝብህን በምትረዳበት ጊዜ እኔንም አስታውሰኝ፤
እነርሱን በምታድንበት ጊዜ እኔንም አስበኝ።
5በአንተ ከሚመኩት ወገኖችህ እንደ አንዱ ሆኜ፥
ሕዝቦችህ ሲበለጽጉ እንዳይና የወገኖችህንም ደስታ እንድካፈል አድርገኝ።
6እንደ ቀድሞ አባቶቻችን ኃጢአት ሠርተናል፤
ተሳስተናል፤ በደለኞችም ሆነናል።
7የቀድሞ አባቶቻችን በግብጽ ምድር
እርሱ ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ አላስተዋሉም፤
ብዙዎቹን የቸርነት ሥራዎቹን አላስታወሱም፤
በቀይ ባሕር አጠገብ ዐመፁ። #ዘፀ. 14፥10-12።
8ሆኖም ኀያል ሥልጣኑን ለማሳወቅ
ስለ ክብሩ አዳናቸው።
9ቀይ ባሕርን በገሠጸው ጊዜ ደረቀ፤
ጥልቁን ውሃ እንደ በረሓ አድርጎ
ሕዝቦቹን እየመራ አሻገራቸው።
10ከሚጠሉአቸውም ሰዎች እጅ አዳናቸው፤
ከጠላቶቻቸውም እጅ ታደጋቸው።
11ጠላቶቻቸውን ግን ውሃው አሰጠማቸው፤
ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት የቀረ አልነበረም።
12ከዚህ በኋላ በተስፋ ቃሉ አመኑ፤
የምስጋናም መዝሙር ዘመሩለት። #ዘፀ. 14፥31። #ዘፀ. 15፥1-21።
13ይሁን እንጂ ያደረገላቸውን ድንቅ ነገር ሁሉ
ወዲያውኑ ረሱ፤
የእርሱንም ምክር ሳይጠብቁ የራሳቸውን ፈቃድ
አደረጉ።
14በበረሓ ሳሉ ብዙ ነገር ተመኙ፤
እግዚአብሔርንም ተፈታተኑት።
15እርሱ የለመኑትን ሁሉ ሰጣቸው፤
ነገር ግን የሚያመነምን በሽታ አመጣባቸው። #ዘኍ. 11፥4-34።
16በበረሓ ሰፍረው ሳሉ በሙሴና
የእግዚአብሔር ቅዱስ አገልጋይ በሆነው በአሮን ቀኑባቸው።
17ምድርም ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤
አቤሮንንና ቤተሰቡንም ከደነቻቸው።
18በተከታዮቻቸውም ላይ እሳት ወረደ፤
እነዚያንም ክፉ ሰዎች አቃጠለ። #ዘኍ. 16፥1-35።
19በኮሬብ ሳሉ የወርቅ ጥጃ ሠሩ፤
ለዚያም ጣዖት ሰገዱ።
20የእግዚአብሔርንም ክብር
ሣር በሚበላ እንስሳ ምስል ለወጡ።
21በግብጽ ሳሉ ታላላቅ ተአምራትን በማድረግ
ያዳናቸውን አምላክ ረሱ።
22በዚያ ሳሉ ያደረገላቸውን አስደናቂ ነገሮችና፥
በቀይ ባሕርም ያደረገላቸውን አስገራሚ ነገሮች ዘነጉ።
23ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሕዝቦቹን
ለማጥፋት ዐቅዶ ነበር፤
ነገር ግን እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ በመካከል በመቆም፥
እንዳያጠፋቸውና ቊጣውንም እንዲመልስ
እግዚአብሔርን ለመነ። #ዘፀ. 32፥1-14።
24በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስላልተማመኑ
መልካሚቷን ምድር ናቁ።
25በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው አጒረመረሙ፤
የእግዚአብሔርንም ቃል አንሰማም አሉ።
26ስለዚህ እጁን አንሥቶ በመማል
በበረሓ የሚያጠፋቸው መሆኑን ነገራቸው፤ #ዘኍ. 14፥1-35።
27ዘሮቻቸውን ሁሉ በአሕዛብ መካከል
እንደሚጥላቸውና በመላው ዓለም እንደሚበታትናቸው ገለጠላቸው። #ዘሌ. 26፥33።
28ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ
በፔዖር የነበረውን ባዓል ተብሎ
የሚጠራውን ጣዖት አመለኩ፤
ሕይወት ለሌላቸው አማልክት
የቀረበውንም የመሥዋዕት ሥጋ በሉ።
29በክፉ ሥራቸው እግዚአብሔርን አስቈጡት፤
በዚህ ምክንያት መቅሠፍት በመካከላቸው ተነሣ።
30ነገር ግን ፊንሐስ ተነሥቶ
በደል የፈጸሙትን በቀጣቸው ጊዜ
መቅሠፍቱ ተወገደ።
31ይህም አድራጎቱ ወደ ፊት ለሚከተለው ትውልድ
ለዘለዓለም እንደ መልካም ሥራ ሆኖ ተቈጠረለት።
32በመሪባ ምንጮች አጠገብ
ሕዝቡ እግዚአብሔርን አስቈጡት፤
በእነርሱም ምክንያት ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ።
33እጅግ አስመርረውት ስለ ነበር
ሙሴ ራሱን ባለመቈጣጠር ተናገረ። #ዘኍ. 20፥2-13።
34እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት
አሕዛብን አላጠፉም፤
35እንዲያውም ከእነርሱ ጋር ተደባልቀው
የኑሮ ሥርዓታቸውን ተከተሉ።
36የእግዚአብሔር ሕዝቦች
የአሕዛብን ጣዖቶች አመለኩ፤
ይህም ለጥፋታቸው ምክንያት ሆነ። #መሳ. 2፥1-3፤ 3፥5-6።
37ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንትና
በከነዓን አገር ለሚገኙ ጣዖቶች
መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። #2ነገ. 17፥17።
38እነርሱ ለከነዓን ጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው
ያቀረቡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በመግደል
ንጹሕ ደም አፍስሰዋል፤ ምድሪቱም በደም ረከሰች። #ዘኍ. 35፥33።
39እነርሱ በሥራቸው ረከሱ፤
በክፉ ሥራቸውም እግዚአብሔርን ካዱ።
40ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተቈጣ፤
እጅግም ተጸየፋቸው። #መሳ. 2፥14-18።
41ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤
ጠላቶቻቸውም ገዥዎቻቸው ሆኑ።
42በጠላቶቻቸው ተጨቊነው
ፈጽሞ የእነርሱ ተገዢዎች ሆኑ።
43እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ታድጎአቸዋል፤
እነርሱ ግን በእርሱ ላይ ማመፅን መረጡ፤
ስለዚህ ኃጢአታቸው ለውድቀታቸው ምክንያት ሆነ።
44ይህም ሁሉ ሆኖ
እንደገና ወደ እግዚአብሔር በሚጮኹበት ጊዜ ይሰማቸው ነበር፤
ሥቃያቸውንም ይመለከት ነበር።
45እነርሱን ለማዳን ቃል ኪዳኑን ያስታውስ ነበር፤
ስለ ታላቅ ፍቅሩም ምሕረት ያደርግላቸው ነበር።
46የሚጨቊኑአቸው ሁሉ
እንዲራሩላቸው አደረገ።
47እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! አድነን!
ከመንግሥታት መካከል መልሰህ
ወደ አገራችን አግባን፤
በዚያን ጊዜ እናመሰግንሃለን፤
ቅዱስ ስምህንም እናከብራለን።
48የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር
ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን!
ሕዝቡ ሁሉ አሜን አሉ፤
እግዚአብሔርንም አመስግኑ። #1ዜ.መ. 16፥35-36።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 106: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997