የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 103:1-18

መጽሐፈ መዝሙር 103:1-18 አማ05

ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! የእግዚአብሔርን ቅዱስ ስም በሙሉ ልቤ አመሰግናለሁ። ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! ቸርነቱንም አትርሺ! ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር ይላል፤ ሕመሜንም ሁሉ ይፈውሳል። ወደ መቃብር ከመውረድ ይጠብቀኛል፤ በፍቅርና በምሕረትም ይባርከኛል። በጐልማሳነቴ ሕይወቴን በመልካም ነገር ሁሉ ይሞላታል፤ እንደ ንስርም ወጣትነቴን ያድሳል። እግዚአብሔር በሚሠራው ሁሉ ጻድቅ ነው፤ ለተጨቈኑት ፍትሕን ይሰጣል። ዕቅዱን ለሙሴ ገለጠለት፤ የእስራኤል ሕዝቦች አስደናቂ ሥራዎቹን እንዲያዩ አደረገ። እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው። በቶሎ የማይቈጣና ለዘለዓለም ታማኝ ነው። ዘወትር የሚገሥጽ አይደለም፤ ቊጣውም ለዘለዓለም አይቈይም። በኃጢአታችን መጠን አልቀጣንም፤ በበደላችንም ልክ አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ የሚለውን ያኽል እግዚአብሔር ለሚፈሩት የሚሰጠው ፍቅር ታላቅ ነው። ምሥራቅ ከምዕራብ የሚርቀውን ያኽል እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ከእኛ ያርቀዋል። አባት ለልጆቹ የሚራራላቸውን ያኽል እግዚአብሔርም የሚፈሩትን ይራራላቸዋል። እግዚአብሔር ከምን እንደ ተፈጠርን ያውቃል፤ ዐፈር መሆናችንንም ያስታውሳል። የሰው ሕይወት እንደ ሣር ነው፤ እንደሚያድግና እንደሚያብብ እንደ ዱር አበባ ነው። የዱር አበባ ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ ወዲያው ይጠፋል፤ በዚያ ስፍራ እንደ ነበረ እንኳ አይታወቅም። ነገር ግን እግዚአብሔር ለሚያከብሩት ሁሉ ፍቅሩን ለዘለዓለም ያሳያቸዋል፤ ቸርነቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። ይህንንም የሚያደርገው ቃል ኪዳኑን ቢጠብቁ፥ ትእዛዙንም በታማኝነት ቢፈጽሙ ነው።