የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 102

102
በመከራ ላይ ያለ ሰው ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ!
የአንተን ርዳታ በመፈለግ ስጮኽም አድምጠኝ!
2መከራ በሚደርስብኝ ጊዜ ከእኔ አትለይ!
አድምጠኝ፤ በምጣራበትም ጊዜ ፈጥነህ ስማኝ!
3የሕይወት ዘመኔ እንደ ጢስ እየበነነ በማለቅ ላይ ነው፤
ሰውነቴም እንደ እሳት እየነደደ ነው።
4እንደ ደረቀ ሣር ተሰባብሬ ደቀቅሁ፤
የምግብ ፍላጎቴም ጠፋ።
5ድምፄን ከፍ አድርጌ በመቃተቴ
ከቈዳና ከአጥንት በቀር ሰውነት የለኝም።
6ብቻውን በበረሓ እንደሚኖር እርኩምና
በወና ቤት እንደሚኖር ጒጒት ሆኜአለሁ።
7እንቅልፍ ከቶ በዐይኔ አይዞርም፤
በቤት ጣራ ላይ እንዳለ ብቸኛ ወፍ ሆኜአለሁ።
8ጠላቶቼ ዘወትር ይሳለቁብኛል፤
ስሜንም መራገሚያ አድርገው ያነሡታል።
9ምግቤ ዐመድ ሆኖአል፤
እንባዬም ከምጠጣው ነገር ጋር ተደባልቆአል፤
10ይህም የሆነው ከፍ ከፍ ካደረግኸኝ በኋላ፥
ከኀይለኛ ቊጣህ የተነሣ ስለ ጣልከኝ ነው።
11የሕይወቴ ዘመን እንደ ማታ ጥላ ሆኖአል፤
እንደ ሣርም እጠወልጋለሁ።
12እግዚአብሔር ሆይ!
አንተ ግን ለዘለዓለም ንጉሥ ነህ፤
ስምህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ገናና ሆኖ ይተላለፋል።
13ለጽዮን ምሕረት የምታደርግላት ጊዜ ስለ ተቃረበና
ጊዜውም አሁን ስለ ሆነ
አንተ ትነሣለህ፤ ለእርስዋም ትራራለህ።
14ድንጋዮችዋ በአገልጋዮችህ ዘንድ የተወደዱ ናቸው፤
ለፍርስራሾችዋ እንኳ ይራራሉ።
15አሕዛብ የእግዚአብሔርን ስም
የምድር ነገሥታትም አንተን ይፈራሉ።
16እግዚአብሔር ጽዮንን እንደገና በሚሠራበት ጊዜ
በክብሩ ይገለጣል።
17የድኾችን ጸሎት ይሰማል፤
ልመናቸውንም አይንቅም።
18ገና ያልተወለዱት ሰዎች እንዲያመሰግኑት
ይህን እግዚአብሔር ያደረገውን ድንቅ ነገር ለሚመጣው ትውልድ ጻፉ።
19እግዚአብሔር በላይ ካለው ከቅዱስ ስፍራው ሆኖ ተመለከተ፤
ከሰማይ ወደ ምድር አየ።
20ይህንንም ያደረገው የእስረኞችን መቃተት ሰምቶ
ሞት የተፈረደባቸውንም ነጻ ለማውጣት ነው።
21ስለዚህ የእግዚአብሔር ስም በጽዮን ይነገራል፤
በኢየሩሳሌምም ይመሰገናል።
22ይህም የሚሆነው ሕዝቦችና መንግሥታት
በአንድነት ተሰብስበው ለእግዚአብሔር በሚሰግዱበት ጊዜ ነው።
23እግዚአብሔር ገና ወጣት ሆኜ ሳለሁ ደካማ አደረገኝ፤
ሕይወቴንም አሳጠረ።
24“አምላክ ሆይ! የአንተ ዘመን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ስለ ሆነ
ዕድሜዬን ሳላጠናቅቅ
በግማሽ ዕድሜዬ አትውሰደኝ” አልኩ።
25አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤
ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው።
26እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤
እነርሱ እንደ ልብስ ያረጃሉ፤
እንደ መጐናጸፊያ ትለውጣቸዋለህ፤ ይወገዱማል።
27አንተ ግን ለዘለዓለም ያው ነህ፤
ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። #ዕብ. 1፥10-12።
28የአገልጋዮችህ ልጆች በሰላም ይኖራሉ፤
ትውልዳቸውም በአንተ ዘንድ ጸንቶ ይኖራል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ