መጽሐፈ ምሳሌ 5:15-23

መጽሐፈ ምሳሌ 5:15-23 አማ05

ከራስህ ጒድጓድና ምንጭ ውሃ ጠጥተህ እንደምትረካ፥ ለሚስትህ ታማኝ በመሆንና እርስዋን ብቻ በመውደድ እርካ። ማንኛዋም ሴት የምትጠጣበት የውሃ ምንጭ አትሁን። ጒድጓድህና ምንጭህ ማንም ሰው ከአንተ ጋር የማይካፈላቸው የአንተ ብቻ ይሁኑ። ስለዚህ በወጣትነት ያገባሃት ሚስትህ እንደ ጥሩ የምንጭ ውሃ ስለ ሆነች ትባረክልህ፤ ከእርስዋም ጋር ደስ ይበልህ። እንደ ተወደደች ዋላ እንድ ተዋበችም ሚዳቋ ትሁንልህ፤ ውበትዋ ሁልጊዜ ያርካህ፤ በፍቅርዋም ዘወትር ደስ ይበልህ። ልጄ ሆይ! በአመንዝራይቱ ሴት ለምን ትማረካለህ? ለምንስ ከሌላው ሰው ሚስት ጋር ትባልጋለህ? እግዚአብሔር ሰው የሚያደርገውን ሁሉ ያያል፤ የሚሄድበትንም መንገድ ሁሉ ይመለከታል። ኃጢአተኛን ሰው የገዛ ራሱ ክፋት ያጠምደዋል፤ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል። ከመጠን በላይ በሆነው ሞኝነቱ መንገዱን ይስታል፤ ራሱን መቈጣጠር ካለመቻሉ የተነሣ ይሞታል።