የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 3

3
ምክር ለወጣቶች
1ልጄ ሆይ! የማስተምርህን አትርሳ፤ ትእዛዞቼንም በልብህ ጠብቅ። 2የእኔ ትምህርት ረጅም ዕድሜን ከብዙ ተድላና ደስታ ጋር ይሰጥሃል። 3ታማኝነትና እውነተኛነትን አትተው፤ እንደ አንገት ሐብል ተጠንቅቀህ ያዛቸው፤ በልብህም ሰሌዳ ጻፋቸው። 4ይህን ብታደርግ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት መወደድንና መልካም ዝናን ታገኛለህ። #ሉቃ. 2፥52።
5በሙሉ ልብህ በእግዚአብሔር ታመን እንጂ በራስህ ዕውቀት አትመካ። 6በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔርን መሪ አድርገው፤ እርሱም በትክክለኛው መንገድ ይመራሃል። 7“እኔ ዐዋቂ ነኝ” አትበል። ይልቅስ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፋትም ራቅ። #ሮም 12፥16። 8ይህን ብታደርግ ለሰውነትህ ጤንነትን፥ ለአጥንቶችህም ጥንካሬን ታገኛለህ። 9ከሀብትህና ምድርህ ከሚያፈራው መልካም ነገር ሁሉ የመጀመሪያውን መባ አድርገህ በመስጠት እግዚአብሔርን አክብር። 10ይህን ብታደርግ ጐተራዎችህ በእህል የተሞሉ ይሆናሉ፤ የወይን መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ሞልቶ ይትረፈረፋል።
11ልጄ ሆይ! የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በሚገሥጽህም ጊዜ አትመረር። #ኢዮብ 5፥17። 12አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ እግዚአብሔርም የሚወዳቸውን ሰዎች ይገሥጻል። #ዕብ. 12፥5-6። #ራዕ. 3፥19። 13ጥበብን የሚያገኝ፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ ሰው የተባረከ ነው። 14ስለዚህ ጥበብ ከብር ይበልጥ ትርፍ ትሰጣለች፤ ከወርቅም የተሻለ ጥቅም ታስገኛለች። 15ጥበብ ከውድ ዕንቊ ትከብራለች፤ አንተ ለማግኘት ከምትመኛቸው ነገሮች ሁሉ እርስዋን የሚወዳደራት ከቶ የለም። 16ጥበብ በቀኝ እጅዋ ረጅም ዕድሜን በግራ እጅዋ ደግሞ ብልጽግናንና ክብርን ይዛለች። 17መንገዶችዋ የደስታ መንገዶች ናቸው፤ መተላለፊያዎችዋም ሁሉ ሰላም የሰፈነባቸው ናቸው። 18ጥበብ፥ ለሚይዟት ሰዎች ሕይወትን ትሰጣለች፤ እርስዋንም ገንዘብ የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው።
19እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤
በማስተዋልም ሰማያትን አጸና።
20በእርሱ ጥበብ ወንዞች ይፈስሳሉ፤
ደመናዎችም ለምድር ዝናብን ይሰጣሉ።
21ልጄ ሆይ! መልካም ጥበብንና አርቆ ማስተዋልን አጥብቀህ ያዝ፤ ከአንተም እንዲርቁ አታድርግ። 22እነርሱም ለአንተ ረጅምና የአማረ ሕይወትን ይሰጡሃል። 23በመንገድህ ያለ ፍርሀት ተማምነህ መሄድ ትችላለህ፤ ከቶም አትሰናከልም። 24በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤ ሌሊቱንም ሙሉ የሰላም እንቅልፍ ታገኛለህ። 25በክፉ ሰዎች ላይ በድንገት የሚደርስ አደጋና ጥፋት ይደርስብኛል ብለህ አትፍራ። 26እግዚአብሔር መታመኛህ ሆኖ በወጥመድም ከመያዝ ይጠብቅሃል።
27ርዳታ እንድታደርግለት ለሚገባው ሰው ዐቅምህ በሚፈቅድልህ መጠን በጎ ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። 28የተቸገረ ጐረቤትህን ዛሬውኑ መርዳት ሲቻልህ “እሺ ነገ” እያልክ አታመላልሰው። 29አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በሚኖረው ጐረቤትህ ላይ በተንኰል ክፉ ነገር ለማድረግ አታስብ። 30ምንም በደል ያላደረሰብህን ሰው ያለ ምክንያት አትክሰሰው። 31በግፈኞች ሰዎች አትቅና፤ ክፉ ሥራቸውንም አትከተል። 32እግዚአብሔር ክፉ አድራጊዎችን ይጠላል፤ ልበ ቅኖችን ግን አጥብቆ ይወዳቸዋል። 33እግዚአብሔር በክፉ ሰዎች ቤት እርግማንን ያመጣል፤ የደጋግ ሰዎችን ቤት ግን ይባርካል። 34እግዚአብሔር ፌዘኞችን ይንቃል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። #ያዕ. 4፥6፤ 1ጴጥ. 5፥5። 35ጠቢባን መልካም ክብርን ያገኛሉ፤ ሞኞች ግን ውርደትን ይከናነባሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ