መጽሐፈ ምሳሌ 26:17-28

መጽሐፈ ምሳሌ 26:17-28 አማ05

በማይመለከትህ ነገር መከራከር በመንገድ የሚተላለፈውን የውሻ ጆሮ እንደ መያዝ ይቈጠራል። ሰውን አታሎ “በቀልድ ነው ያደረግኹት” የሚል ሰው በአደገኛ የጦር መሣሪያ እንደሚጫወት ዕብድ ሰው ነው። እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ አሾክሿኪ ከሌለም ጠብ ይቆማል። ከሰል ፍምን፥ እንጨትም እሳትን እንደሚያበዛ ጠብ አጫሪ ሰው ጠብን ያባብሳል። የአሾክሻኪ ቃል እንደ ጣፋጭ ምግብ ደስ እያሰኘ እስከ ውስጥ ሰውነት ይወርዳል። በልቡ ክፋት እያለ በአንደበቱ ልዝብ ቃል የሚናገር ሰው ውጪው በሚያምር በብር ቀለም እንደ ተቀባ የሸክላ ዕቃ ነው። ተንኰለኛ ሰው በአፉ ይሸነግላል፤ በልቡ ግን ተንኰልን ያውጠነጥናል። እርሱም ልቡ በጥላቻ የተሞላ ስለ ሆነ፤ በሚያባብል ቃል ቢያቈላምጥህም አትመነው፤ ጥላቻውን ቢሰውርም፥ የሚያደርገው ክፉ ነገር በሰው ሁሉ ዘንድ ግልጥ ነው። ለሌሎች ወጥመድን የሚዘረጉ ሰዎች ራሳቸው ይያዙበታል፤ በሰው ላይ የሚሰዱት የድንጋይ ናዳ እነርሱን መልሶ ይጐዳቸዋል። ዋሾ አንደበት የሚጐዳቸውን ሰዎች ይጠላል፤ የሽንገላ ንግግርም ጥፋትን ያመጣል።