መጽሐፈ ምሳሌ 22
22
1መልካም ስም ከብዙ ሃብት ይሻላል፤
በሰው ዘንድ መወደድም ከብር ወይም ከወርቅ ይበልጣል።
2ሀብታምንም ሆነ ድኻን የፈጠራቸው እግዚአብሔር ስለ ሆነ
ሁለቱም በዚህ አንድ ናቸው።
3ብልኅ ሰው አደጋ ሲመጣ አይቶ ይሸሸጋል።
ማስተዋል የጐደለው ሰው ግን ሰተት ብሎ ወደ መከራ በመግባት ይጐዳል።
4እግዚአብሔርን መፍራትና ትሑት መሆን
ሀብት፥ ክብርና ሕይወትን ያስገኛል።
5በክፉዎች መንገድ ላይ እሾኽና ወጥመድ አለ፤
ራሱን የሚጠብቅ ግን ከእነርሱ ይርቃል።
6ልጅን እንዴት መኖር እንደሚገባው ብታስተምረው
በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።
7ድኻ የሀብታም ሰው አገልጋይ ነው፤
ገንዘብ የሚበደር የአበዳሪው ባሪያ ነው።
8ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፤
ቊጣውም የትም አያደርሰውም።
9ምግቡን ከድኾች ጋር ስለሚካፈል
ለጋሥ ሰው የተባረከ ይሆናል።
10ፌዘኛን ሰው ብታስወጣ ጠብ ይቆማል፤
ጠብና ስድብም አይኖሩም።
11የልብ ንጽሕናንና መልካም ንግግርን የሚወድ ሰው
በንጉሥ ዘንድ የተወደደ ይሆናል።
12የእግዚአብሔር ዐይኖች ዕውቀትን ይጠብቃሉ፤
እምነት የሌላቸውን ሰዎች ዕቅድ ግን ያስወግዳል።
13ሰነፍ ሰው “ውጪ አንበሳ አለ፤ ብወጣ ይገድለኛል” ብሎ ይከራከራል።
“አንበሳ ያገኘኛል” በማለት ከቤቱ አይወጣም።
14የአመንዝራ ሴት አፍ እንደ ጥልቅ ጒድጓድ ነው።
እግዚአብሔር የጠላቸው ሰዎችም ተይዘው ይወድቁበታል።
15በልጅ ልብ ውስጥ ሞኝነት አለ፤
የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያስወግደዋል።
16ለሀብታሞች ስጦታ የሚሰጥ፥
ወይም ሀብት ለማግኘት ብሎ ድኾችን የሚጨቊን ሰው ይደኸያል።
ሠላሳ የጥበብ ምክሮች
17ጠቢባን ሰዎች የተናገሩትን ሳስተምርህ አድምጥ፤ ከእነርሱ የምታገኘውን ትምህርት አጥና፤ 18ዘወትር ብታስታውሳቸውና ብትጠቀምባቸው ደስ ይሉሃል፤ 19እነርሱንም የማስተላልፍልህ እምነትህ በእግዚአብሔር እንዲሆን ብዬ ነው። 20እነሆ ሠላሳ መመሪያዎችን ጽፌልሃለሁ፤ እነርሱ ዕውቀትና መልካም ምክር የሚገኙባቸው ናቸው፤ 21እውነት ምን እንደ ሆነም ያስተምሩሃል፤ “እውነትን ፈልገህ አቅርብ” ተብለህ ብትጠየቅም ትክክለኛውን መልስ ትሰጣለህ።
-1-
22ምንም ስለሌላቸው፥ ድኾችን አትበዝብዝ፤ የተጨቈኑትንም ሰዎች በፍርድ ሸንጎ አታጒላላ፤ 23ይኸውም እግዚአብሔር ስለሚከራከርላቸውና የሚያስጨንቁአቸውንም ስለሚያስጨንቅ ነው።
-2-
24ከንዴተኛና ከቊጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፤ 25የእርሱን ጠባይ ከተማርክ አትላቀቅም።
-3-
26የሌላ ሰው ዕዳ ለመክፈል ዋስ አትሁን፤ 27መክፈል ባትችል የምትተኛበት አልጋ እንኳ ሳይቀር ያለህ ንብረት ሁሉ ይወስድብሃል።
-4-
28የቀድሞ አባቶችህ ያኖሩትን የወሰን ምልክት አትለውጥ።
-5-
29በሥራው የሠለጠነ ሰው ታያለህን? እንደዚህ ያለ ሰው በተራ ሰው ፊት ሳይሆን በነገሥታት ፊት ለአገልግሎት ይቆማል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 22: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997