መጽሐፈ ምሳሌ 20:22-30

መጽሐፈ ምሳሌ 20:22-30 አማ05

ክፉ ያደረገብህን ሰው አንተም መልሰህ ክፉ አታድርግበት፤ በእግዚአብሔር ታመን፤ እርሱም ይታደግሃል። እግዚአብሔር ያልተስተካከለ መስፈሪያና ሐሰተኛ ሚዛን ይጸየፋል። እግዚአብሔር የምንራመድበትን መንገድ ወስኖአል፤ ታዲያ፥ ሰው ሕይወቱ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመራ እንዴት ሊያውቅ ይችላል? በኋላ እንዳትጸጸት ለእግዚአብሔር ከመሳልህ በፊት ተጠንቅቀህ አስብ። ብልኅ ንጉሥ ዐመፀኞችን ለይቶ ያውቃቸዋል፤ ያለ ምሕረትም ይቀጣቸዋል። የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ስለ ሆነ የሰውን ውስጣዊ ሰውነት ሁሉ ይመረምራል። ቸርነትና ታማኝነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤ መንግሥቱም በእውነተኛነት ላይ ጸንቶ ይኖራል። የወጣቶች መመኪያ ብርታታቸው ነው፤ የሽማግሌዎችም መከበሪያ ሽበታቸው ነው። የሚያቈስል ቅጣት ክፉ ነገርን ያስወግዳል፤ ግርፋትም የሰውን ውስጣዊ ሁኔታ ያነጻል።