መጽሐፈ ምሳሌ 20
20
1ወይን ጠጅ ፌዘኛ፥ ጠንካራ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋሉ፤
በእነርሱ ሱስ የተጠመደ ጥበበኛ ሊሆን አይችልም።
2የንጉሥ ቊጣ እንደሚያገሣው አንበሳ ያስፈራል፤
የእርሱንም ቊጣ የሚያነሣሣ
በራሱ ላይ የሞት ፍርድ እንደ ፈረደ ይቈጠራል።
3ማንኛውም ሞኝ ተቈጥቶ ጠብ ማነሣሣት ይችላል፤
ሰውን የሚያስከብረው ግን ከክርክር መራቅ ነው።
4መሬቱን በወቅቱ የማያርስ ሰነፍ ገበሬ
በመከር ጊዜ የሚሰበስበው ምርት አይኖረውም።
5የሰው ሐሳብ በጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ እንዳለ ውሃ ነው፤
ይሁን እንጂ ማስተዋል ያለው ሰው ይቀዳዋል።
6ሰው ሁሉ ስለ ራሱ ደግነት ያወራል፤
ነገር ግን በእውነት ታማኝ የሆነውን ሰው
ማን ሊያገኝ ይችላል!
7ጻድቅ ሰው በቅንነት ይኖራል፤
የእርሱ ልጆችም የተባረኩ ናቸው።
8በፍርድ ዙፋን ላይ የተቀመጠ ንጉሥ
ክፉ የሆነውን ነገር ሁሉ አበጥሮ የሚያውቅ ዐይን አለው።
9“ኅሊናዬ ንጹሕ ነው፤
ኃጢአትም የለብኝም”
ማለት የሚችል ሰው ይኖራልን?
10እግዚአብሔር በሐሰተኛ ሚዛንና ትክክል ባልሆነ መስፈሪያ
የሚጠቀሙ ሰዎችን ይጠላል።
11ሕፃን እንኳ ደግና ቅን መሆኑ
በሚያደርገው ነገር ይታወቃል።
12የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዐይንን
የፈጠረ እግዚአብሔር ነው።
13ጊዜህን በእንቅልፍ ብትጨርስ ትደኸያለህ፤
ተግተህ ብትሠራ ግን በቂ ምግብ ይኖርሃል።
14ገዢ ዘወትር መጥፎ ነው እያለ ዕቃን ያራክሳል፤
ገዝቶ ከሄደ በኋላ ግን “በርካሽ ገዛሁ” እያለ ይመካል።
15ዕውቀት የተሞላበት ንግግር፥
ከወርቅና ከከበረ ዕንቊ ይበልጥ የተወደደ ነው።
16ማንም ሰው ለእንግዳ ሰው ከተዋሰ፥ ልብሱን ውሰድ፤
ለማይታወቀው ሰው መያዣ እንዲሆን አንተ ዘንድ አስቀምጠው።
17በማጭበርበር የምታገኘው ነገር
እንደ ጣፋጭ ምግብ ሊያስደስትህ ይችላል፤
ነገር ግን ውሎ ሲያድር በአፍ ውስጥ እንደ አሸዋ ይሆናል።
18መልካም ምክርን ብትቀበል
ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤
ስለዚህ መልካም ምክር ሳትቀበል ወደ ጦርነት አትሂድ።
19ሐሜተኛ ሰው ምሥጢር አይደብቅም፤
ስለዚህ በከንቱ ከሚለፈልፉ ሰዎች ራቅ።
20አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ
ሕይወቱ በድቅድቅ ጨለማ ጊዜ እንደሚጠፋ መብራት ይሆናል።
21በመጀመሪያ ያለ ድካም በቀላሉ የሚገኝ ሀብት
በመጨረሻ አይባረክም።
22ክፉ ያደረገብህን ሰው አንተም መልሰህ
ክፉ አታድርግበት፤
በእግዚአብሔር ታመን፤ እርሱም ይታደግሃል።
23እግዚአብሔር ያልተስተካከለ መስፈሪያና
ሐሰተኛ ሚዛን ይጸየፋል።
24እግዚአብሔር የምንራመድበትን መንገድ ወስኖአል፤
ታዲያ፥ ሰው ሕይወቱ ወዴት አቅጣጫ
እንደሚያመራ እንዴት ሊያውቅ ይችላል?
25በኋላ እንዳትጸጸት ለእግዚአብሔር ከመሳልህ በፊት
ተጠንቅቀህ አስብ።
26ብልኅ ንጉሥ ዐመፀኞችን ለይቶ ያውቃቸዋል፤
ያለ ምሕረትም ይቀጣቸዋል።
27የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ስለ ሆነ
የሰውን ውስጣዊ ሰውነት ሁሉ ይመረምራል።
28ቸርነትና ታማኝነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤
መንግሥቱም በእውነተኛነት ላይ ጸንቶ ይኖራል።
29የወጣቶች መመኪያ ብርታታቸው ነው፤
የሽማግሌዎችም መከበሪያ ሽበታቸው ነው።
30የሚያቈስል ቅጣት ክፉ ነገርን ያስወግዳል፤
ግርፋትም የሰውን ውስጣዊ ሁኔታ ያነጻል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 20: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997