የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 13

13
1ብልኅ ልጅ የአባቱን ምክር ይቀበላል፤
ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም።
2ደጋግ ሰዎች የመልካም አነጋገራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤
የአታላዮች ምኞት ግን የግፍ ሥራ ለመፈጸም ነው።
3ተጠንቅቆ የሚናገር ሕይወቱን ይጠብቃል።
ግዴለሽ ተናጋሪ ግን ጥፋት ይደርስበታል።
4ሰነፍ አንድ ነገር ለማግኘት አጥብቆ ይመኛል፤
ይሁን እንጂ አያገኝም፤
ትጉህ ሠራተኛ ግን የሚፈልገውን ሁሉ ያገኛል።
5ደጋግ ሰዎች ሐሰትን ይጠላሉ፤
የክፉዎች ሰዎች ንግግር ግን አሳፋሪና አስነዋሪ ነው።
6ደጋግ ሰዎች ደግነታቸው ይጠብቃቸዋል፤
ኃጢአተኞችን ግን ኃጢአታቸው ያጠፋቸዋል።
7አንዳንድ ሰዎች ምንም ሳይኖራቸው ሀብታም መስለው ለመታየት ይጥራሉ፤
ሌሎች ደግሞ ብዙ ሀብት እያላቸው፥ ምንም ሀብት እንደሌላቸው መስለው ይኖራሉ።
8ሀብታም በገንዘብ ሕይወቱን ለማዳን ይጣጣራል፤
ድኻ ግን የሚወሰድበት ሀብት ስለሌለው አይጨነቅም።
9የጻድቃን ብርሃን ያንጸባርቃል፤
የኃጢአተኞች መብራት ግን ይጠፋል።
10ትዕቢት ጠብን ያመጣል፤
ምክርን መጠየቅ ግን ብልኅነት ነው።
11ያለ ድካም በቀላሉ የተገኘ ሀብት ወዲያው ይጠፋል፤
ተግቶ በመሥራት የተገኘ ሀብት ግን እየበዛ ይሄዳል።
12ተስፋ ሲዘገይ ልብን ያሳዝናል፤
የተመኙት ነገር ሲፈጸም ግን ደስ ያሰኛል።
13መልካም ምክርን የሚንቅ ችግር ይደርስበታል፤
ትእዛዝን የሚያከብር ግን ዋጋ ያገኝበታል።
14የጠቢባን ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው፤
ሕይወትህ በአደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳ እንድታመልጥ ይረዳሃል።
15አስተዋይ መሆን ያስከብራል፤
ከዳተኛነት ግን ወደ ጥፋት ያደርሳል።
16አስተዋይ ሰዎች ለሚሠሩት ሥራ አስቀድመው ዕቅድ ያወጣሉ፤
ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን አላዋቂነታቸውን ይገልጣሉ።
17ክፉ መልእክተኛ ችግርን ያመጣል፤
ታማኝ መልእክተኛ ግን ሰላምን ያስገኛል።
18ትምህርት የማይወድ ሰው፥ ድኽነትና ውርደት ይገጥመዋል፤
ተግሣጽን የሚቀበል ግን ይከበራል።
19የተመኙትን ነገር ማግኘት እጅግ ደስ ያሰኛል፤
ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን ከክፉ ነገር መራቅ አይፈልጉም።
20ከጥበበኞች የሚወዳጅ ጥበበኛ ይሆናል።
ማስተዋል ከጐደላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ የሚሆን ግን ይጐዳል።
21ኃጢአተኞችን በሄዱበት ስፍራ ሁሉ መከራ ይከተላቸዋል፤
ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ።
22ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ የሚተላለፍ ሀብት ያገኛል፤
የኃጢአተኞችን ሀብት ግን ቅን ሰዎች ይወርሱታል።
23የድኻ እርሻ የተትረፈረፈ ምርትን ሊያስገኝ ይችል ይሆናል።
ከፍርድ መጓደል የተነሣ ግን ይጠፋል።
24ልጁን የማይቀጣ አይወደውም ማለት ነው፤
ልጁን የሚወድ ግን ቀጥቶ ያሳድገዋል።
25እውነተኞች ሊበሉ የሚፈልጉትን ያኽል ያገኛሉ።
ኃጢአተኞች ግን ዘወትር ይራባሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ