የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ የደስታዬና የሥራዬ አክሊል የሆናችሁ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ጸንታችሁ ኑሩ። ኤዎድያና ሲንጢኪ እርስ በርሳቸው በጌታ ተስማምተው እንዲኖሩ እለምናቸዋለሁ። አንተም እዚያ ያለኸው ታማኝ የሥራ ጓደኛዬ እነዚህን ሴቶች እንድትረዳቸው እለምንሃለሁ፤ እነዚህ ሴቶች ከእኔ ጋር ከቀሌምንጦስና ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከሌሎችም የሥራ ጓደኞቼ ጋር በመሆን ወንጌልን በማዳረስ ረገድ ተጋድለዋል። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜም “ደስ ይበላችሁ!” እላለሁ። ደግነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ተመልሶ ሊመጣ ቀርቦአል፤ ስለዚህ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎት፥ በልመናና በምስጋና ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ ስለምንም ነገር አትጨነቁ። ከሰው ማስተዋል ሁሉ በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አእምሮአችሁን በኢየሱስ ክርስቶስ ይጠብቃል። አእምሮአችሁ በእነዚህ ከሁሉ በሚበልጡና በሚያስመሰግኑ መልካም ነገሮች የተመላ ይሁን፤ በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ! እውነተኛ፥ ክቡር፥ ትክክለኛ፥ ንጹሕ፥ አስደሳችና ምስጉን የሆኑ ነገሮችን ሁሉ አስቡ። ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን፥ የሰማችሁትንና ያያችሁትን ሁሉ አድርጉ፤ የሰላም አምላክም ከእናንተ ጋር ይሆናል። ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደገና ለእኔ ችግር ማሰብ ስለ ጀመራችሁ በጌታ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፤ ይህንንም ስል የአሰባችሁትን በሥራ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ አላገኛችሁም ነበር ማለቴ ነው እንጂ ስለ እኔ ችግር ማሰባችሁን አቋርጣችኋል ማለቴ አይደለም። ደግሞም ይህን የምለው ለኑሮዬ የሚያስፈልገኝን በማጣቴ አይደለም፤ እኔማ “ያለኝ ነገር ይበቃኛል” ማለትን ተምሬአለሁ። ስለዚህ ማግኘትንም ሆነ ማጣትን ዐውቃለሁ፤ በማንኛውም ቦታ ሆነ በየትኛውም ጊዜ የመጥገብንና የመራብን፥ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos