ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4
4
የመጨረሻ ምክር
1የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ የደስታዬና የሥራዬ አክሊል የሆናችሁ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ጸንታችሁ ኑሩ።
2ኤዎድያና ሲንጢኪ እርስ በርሳቸው በጌታ ተስማምተው እንዲኖሩ እለምናቸዋለሁ። 3አንተም እዚያ ያለኸው ታማኝ የሥራ ጓደኛዬ እነዚህን ሴቶች እንድትረዳቸው እለምንሃለሁ፤ እነዚህ ሴቶች ከእኔ ጋር ከቀሌምንጦስና ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከሌሎችም የሥራ ጓደኞቼ ጋር በመሆን ወንጌልን በማዳረስ ረገድ ተጋድለዋል።
4ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜም “ደስ ይበላችሁ!” እላለሁ።
5ደግነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ተመልሶ ሊመጣ ቀርቦአል፤ 6ስለዚህ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎት፥ በልመናና በምስጋና ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ ስለምንም ነገር አትጨነቁ። 7ከሰው ማስተዋል ሁሉ በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አእምሮአችሁን በኢየሱስ ክርስቶስ ይጠብቃል።
8አእምሮአችሁ በእነዚህ ከሁሉ በሚበልጡና በሚያስመሰግኑ መልካም ነገሮች የተመላ ይሁን፤ በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ! እውነተኛ፥ ክቡር፥ ትክክለኛ፥ ንጹሕ፥ አስደሳችና ምስጉን የሆኑ ነገሮችን ሁሉ አስቡ። 9ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን፥ የሰማችሁትንና ያያችሁትን ሁሉ አድርጉ፤ የሰላም አምላክም ከእናንተ ጋር ይሆናል።
ጳውሎስ ስለ ተላከለት ስጦታ ማመስገኑ
10ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደገና ለእኔ ችግር ማሰብ ስለ ጀመራችሁ በጌታ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፤ ይህንንም ስል የአሰባችሁትን በሥራ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ አላገኛችሁም ነበር ማለቴ ነው እንጂ ስለ እኔ ችግር ማሰባችሁን አቋርጣችኋል ማለቴ አይደለም። 11ደግሞም ይህን የምለው ለኑሮዬ የሚያስፈልገኝን በማጣቴ አይደለም፤ እኔማ “ያለኝ ነገር ይበቃኛል” ማለትን ተምሬአለሁ። 12ስለዚህ ማግኘትንም ሆነ ማጣትን ዐውቃለሁ፤ በማንኛውም ቦታ ሆነ በየትኛውም ጊዜ የመጥገብንና የመራብን፥ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። 13ኀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ።
14ይሁን እንጂ እናንተ የችግሬ ተካፋዮች ሆናችሁ በመገኘታችሁ መልካም አደረጋችሁ። 15ከዚህም በቀር ወንጌልን ለማብሠር በጀመርኩበት ጊዜ ከመቄዶንያ ስወጣ ከእናንተ በፊልጵስዩስ ከምትገኙት አማኞች በቀር በመስጠትም ሆነ በመቀበል ከእኔ ጋር የተባበረ ሌላ ማኅበረ ምእመናን እንዳልነበረ እናንተው ራሳችሁ ታውቃላችሁ። #2ቆሮ. 11፥9። 16በተሰሎንቄም ችግር እንደ ደረሰብኝ ዐውቃችሁ መላልሳችሁ ርዳታ ልካችሁልኛል። #ሐ.ሥ. 17፥1። 17ይህንንም ስል የእናንተን ስጦታ ለማግኘት በመጓጓት ሳይሆን የልግሥናችሁ ፍሬ እንዲበዛላችሁ በመመኘት ነው። 18የሚያስፈልገኝንና ከሚያስፈልገኝም በላይ የላካችሁልኝን ስጦታ ከኤጳፍሮዲቱስ እጅ ተቀብዬአለሁ፤ ይህም የእናንተ ስጦታ በመልካም መዓዛ እንደ ተሞላ መሥዋዕት እግዚአብሔር የሚቀበለውና ደስ የሚሰኝበት ነው። #ዘፀ. 29፥18። 19ስለዚህም አምላኬ ከክብሩ ብልጽግና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሰጣችኋል። 20ለአባታችንና ለአምላካችን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
የመጨረሻ ሰላምታ
21ለምእመናን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22ሌሎችም አማኞች ሁሉ በተለይም ከሮማው ንጉሠ ነገሥት ቤተሰቦች የሆኑት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
23የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
Currently Selected:
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997