ኦሪት ዘኊልቊ 8:1-14

ኦሪት ዘኊልቊ 8:1-14 አማ05

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሰባቱን መብራቶች በመቅረዙ ላይ በሚያኖርበት ጊዜ ብርሃኑ ፊት ለፊት እንዲበራ አድርጎ ያስቀምጣቸው ዘንድ ለአሮን ንገረው።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አሮንም እንዲህ አደረገ፤ በመቅረዙ ፊት ለፊት እንዲበሩ በማድረግም መብራቶቹን አኖረ። መቅረዙም እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ዕቅድ መሠረት እስከ አገዳውና አበባው ድረስ ከተቀጠቀጠ ወርቅ የተሠራ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከቀሩት የእስራኤል ሕዝብ መካከል ሌዋውያንን ለይተህ እንዲነጹ አድርግ፤ ለመንጻት ሥርዓት በተዘጋጀው ውሃ እርጫቸው፤ በሰውነታቸው ላይ ያለውን ጠጒር ሁሉ እንዲላጩና ልብሳቸውንም አጥበው ራሳቸውን እንዲያነጹ አድርግ፤ ቀጥሎም አንድ ወይፈንና ለእህል ቊርባን የተመደበውን በዘይት የተለወሰ ዱቄት ይውሰዱ፤ አንተም ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርብ አንድ ወይፈን ውሰድ፤ ከዚያን በኋላ የእስራኤልን ሕዝብ ሰብስበህ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ፊት እንዲቆሙ አድርግ። እስራኤላውያን እጆቻቸውን በሌዋውያን ራስ ላይ ይጫኑ፤ ሌዋውያን ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ለእኔ ለእግዚአብሔር እንደ ልዩ ስጦታ ሆነው በመቅረብ ያገለግሉኝ ዘንድ አሮን ይቀድሳቸዋል። ከዚህ በኋላ ሌዋውያን እጆቻቸውን በሁለቱ ኰርማዎች ላይ ይጭናሉ፤ አንዱ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት፥ ሌላው የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል፤ ለሌዋውያን ለማስተስረይ የሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት በዚህ ዐይነት ይከናወናል።” “ሌዋውያንን ለእኔ የተለየ ስጦታ አድርገህ ቀድስልኝ፤ አሮንንና ልጆቹንም በእነርሱ ላይ ሹማቸው፤ በዚህም ዐይነት ሌዋውያን የኔ ይሆኑ ዘንድ ከቀሩት የእስራኤል ሕዝብ መካከል ለይልኝ፤