ኦሪት ዘኊልቊ 4
4
የቀዓት ጐሣዎች ተግባር
1እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2“ከሌዊ ልጆች መካከል የቀዓትን ዘር በየቤተሰባቸውና በየጐሣቸው ቊጠር፤ 3በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል ብቃት ያላቸውን፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ የሚደርሰውን ወንዶች ሁሉ መዝግብ። 4የእነርሱም አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙትን ንዋያተ ቅድሳት መንከባከብ ይሆናል።
5“ሕዝቡ ከሰፈረበት ቦታ በሚነሣበት ጊዜ አሮንና ልጆቹ ወደ ድንኳኑ ገብተው፥ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ያለውን መጋረጃ በማውረድ የኪዳኑን ታቦት በእርሱ ይጠቅልሉት። 6የተለፋውንም የቊርበት መሸፈኛ በመጋረጃው ላይ አድርገው በዚያም ላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ዘርግተው ያልብሱት፤ መሎጊያዎችንም ያስገቡ።
7“ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የተቀደሰ ኅብስት ማኖሪያ የሆነውንም ገበታ በሰማያዊ ጨርቅ ይሸፍኑት፤ በገበታውም ላይ ሳሕኖችን፥ ጭልፋዎችን፥ ጽዋዎችንና የወይን ጠጅ መቅጃዎችን ያኑሩ፤ ኅብስትም ዘወትር በእርሱ ላይ ይኑርበት። 8ይህን ሁሉ በቀይ ጨርቅ ሸፍነው ከበላዩ የተለፋ ስስ ቊርበት ይደርቡ፤ መሎጊያዎችንም ያስገቡ።
9“ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው መቅረዙን፥ ከነመብራቶቹ ከመኮስተሪያዎቹና ከኩስታሪ ማኖሪያዎቹ፥ እንዲሁም ከዘይት ዕቃዎቹ ሁሉ ጋር ይሸፍኑት። 10መቅረዙንና የእርሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ በቈዳ መሸፈኛ ጠቅልለው በመሸከሚያ ተራዳ ላይ ያኑሩት።
11“ቀጥሎም የወርቁን መሠዊያ በሰማያዊ ጨርቅ ሸፍነው የተለፋ ስስ ቊርበት በላዩ ያድርጉ፤ መሎጊያዎችንም ያስገቡበት። 12በመቅደሱ መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች ሁሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ ይሸፍኑአቸው፤ የለፋ ስስ ቊርበት ደርበውም በመሸከሚያው ተራዳ ላይ ያኑሩአቸው። 13ዐመዱንም ከመሠዊያው ላይ ከጠረጉ በኋላ መሠዊያውን በሐምራዊ ጨርቅ ይሸፍኑት። 14በመሠዊያው ላይ ለማገልገል የሚጠቅሙትን ዕቃዎች፥ ማለትም ማንደጃዎችን፥ ሜንጦዎችን፥ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ያስቀምጡበት፤ የተለፋውንም ስስ ቊርበት በላዩ ደርበው መሎጊያዎችን ያስገቡበት። 15ከሰፈር በሚነሡበትም ጊዜ አሮንና ልጆቹ ንዋያተ ቅድሳቱንና የእነርሱንም መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ የቀዓት ልጆች መጥተው ይሸከሙአቸው፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋያተ ቅድሳቱን መንካት አይገባቸውም፤ እንግዲህ የመገናኛው ድንኳን በሚነሣበት ጊዜ ሁሉ የቀዓት ልጆች ኀላፊነት ይህ ነው።
16“የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፥ ጣፋጭ ሽታ ባለው ዕጣን፥ ዘወትር በሚቀርበው በእህሉ ቊርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን በሙሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዕቃ ሁሉ ይጠብቃል።”
17እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 18“የቀዓትን ልጆች ከሌዋውያን ነገድ መካከል ተቀሥፈው እንዲጠፉ አታድርጉ፤ 19ወደ ተቀደሰው ስፍራ ተጠግተው እንዳይሞቱ እንዲህ አድርግላቸው፦ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ገብተው የያንዳንዱን ሰው ሥራና ሸክሙን ይመድቡለት። 20ነገር ግን እንዳይሞቱ የቀዓት ልጆች ወደ ድንኳኑ ውስጥ ገብተው ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይድፈሩ።”
የጌርሾን ጐሣዎች ተግባር
21እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 22“የጌርሾን ጐሣዎች የሆኑትን ሌዋውያን በየትውልዳቸውና በየቤተሰባቸው ቊጠራቸው፤ 23በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል ብቃት ያላቸውን፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠር፤ 24እነርሱ ልዩ ልዩ ዕቃዎችን የመሸከም ኀላፊነት ይኖራቸዋል። 25የመገናኛውን ድንኳን የውስጥና የውጪ መሸፈኛ፥ ከላይ የሚደረበውን የተለፋ ስስ ቊርበት፥ የመግቢያውን በር መጋረጃ ይሸከማሉ፤ 26እንዲሁም በድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ለሚገኘው አደባባይ የተሠሩትን መጋረጃዎችና አውታሮች፥ ለአደባባዩ መግቢያ በር የሚሆኑትን መጋረጃዎችና ለእነዚህ መገልገያ የተመደቡትን ሌሎችንም ዕቃዎች ሁሉ ይሸከማሉ፤ ለእነዚህም ዕቃዎች የሚሆነውን ማንኛውንም አገልግሎት ይፈጽማሉ። 27በሚሸከሙአቸው ነገሮችና በሚሠሩአቸው ሥራዎች የጌርሾንን ልጆች አገልግሎት አሮንና ልጆቹ ይቈጣጠሩአቸዋል፤ መሸከም ያለባቸውንም ነገሮች ሁሉ ትመድብላቸዋለህ። 28በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የጌርሾን ልጆች አገልግሎት ይህ ነው፤ ሥራቸውንም የካህኑ የአሮን ልጅ ኢታማር ይቈጣጠራል።
የሜራሪ ጐሣዎች ተግባር
29“የሜራሪ ዘሮች የሆኑትን ሌዋውያን በየትውልዳቸው፥ በየቤተሰባቸው ቊጠራቸው፤ 30በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል ብቃት ያላቸውን፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠር፤ 31እነርሱ መሸከም ያለባቸው ተራዳዎችን፥ መወርወሪያዎችን፥ ምሰሶችን፥ የማደሪያው ድንኳን የሚቆምባቸውን እግሮች፥ 32እንዲሁም በድንኳኑ ዙሪያ የሚገኘውን አደባባይ ምሰሶችን፥ እግሮቻቸውን፥ ካስማዎችን፥ አውታሮችንና ለእነዚህ ሁሉ መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች ነው፤ እያንዳንዱም መሸከም ያለበትን ዕቃ በየስሙ ትመድብለታለህ። 33በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር ተቈጣጣሪነት የሚካሄደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሜራሪ ልጆች ቤተሰብ አገልግሎት ይህ ነው።”
የሌዋውያን ብዛት
34ሙሴ፥ አሮንና የሕዝቡ አለቆች የቀዓትን ዘሮች በየወገናቸው፥ በየቤተሰባቸው ቈጠሩአቸው፤ 35በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገልግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ያሉትን ቈጠሩአቸው፤ 36የተቈጠሩት ብዛታቸው ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ኀምሳ ነበር፤ 37እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉትና ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው የቀዓት ቤተሰቦች ሁሉ እነዚህ ነበሩ።
38በየቤተሰባቸውና በየወገናቸው የተቈጠሩት የጌርሾን ልጆች፥ 39በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል መግባት የቻሉ፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሚሆን ሁሉ፥ 40ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 41እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉትና ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው የጌርሾን ልጆች እነዚህ ናቸው።
42በየቤተሰባቸውና በየወገናቸው የተቈጠሩት የሜራሪ ልጆች፥ 43በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል መግባት የቻሉ፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሚሆን ሁሉ 44ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበር። 45እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉትና ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው የሜራሪ ልጆች እነዚህ ናቸው። 46ሙሴ አሮንና የእስራኤል አለቆች በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች የቈጠሩአቸው ሌዋውያን፥ 47ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትና በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራት፥ ዕቃውን ለመሸከም የገቡት፥ 48ጠቅላላ ቊጥራቸው ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሰማኒያ ነበር።
49በዚህም ዐይነት እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ተቈጠረ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ የማገልገልንና የመሸከምን ኀላፊነት ተቀበለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997