ኦሪት ዘኊልቊ 3:1-10

ኦሪት ዘኊልቊ 3:1-10 አማ05

እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር። አሮን አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኲሩ ናዳብ ሲሆን የቀሩት አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ነበሩ። እነዚህም በክህነት እንዲያገለግሉ ተቀብተው ነበር። ነገር ግን ከእነርሱ ውስጥ ናዳብና አቢሁ በሲና በረሓ በእግዚአብሔር ፊት ያልተቀደሰ እሳት ጭረው በማቅረባቸው ተቀሥፈው ሞቱ፤ እነርሱም ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህም አልዓዛርና ኢታማር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በክህነት ያገለግሉ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የሌዊን ነገድ አቅርበህ ለካህኑ አሮን አገልጋዮች እንዲሆኑ መድባቸው፤ እነርሱም አሮንንና መላውን ማኅበር በመገናኛው ድንኳን በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚገኙ መገልገያ ዕቃዎች ኀላፊዎች ይሆናሉ። እስራኤላውያንንም በድንኳኑ ውስጥ በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። ከእስራኤላውያን ሁሉ ተለይተው ለአሮንና ለልጆቹ ያገለግሉ ዘንድ ሌዋውያንን መድባቸው። የክህነቱንም ሥራ ያከናውኑ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ ከእነርሱ በቀር ሌላ ሰው ይህን ሥራ ለማከናወን ቢሞክር በሞት ይቀጣ።”