ዘኍልቍ 3:1-10
ዘኍልቍ 3:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። በክህነት ያገለግሉ ዘንድ የተቀቡና እጆቻቸውን የተቀደሱ የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው። ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ከሌላ እሳት ጭረው አምጥተዋልና በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር ከአባታቸው ከአሮን ጋር በክህነት ያገለግሉ ነበር። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። የድንኳኑን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሕጉንና የእስራኤልን ልጆች ሕግ በምስክሩ ድንኳን ፊት ይጠብቁ። እንደ ድንኳኑ ሥራዎች ሁሉ የምስክሩን ድንኳን ዕቃና የእስራኤልን ልጆች ሕግ ይጠብቁ። ሌዋውያንንም ወደ ወንድምህ ወደ አሮንና ወደ ልጆቹ ወደ ካህናቱ ታገባቸዋለህ። ከእስራኤል ልጆች ተለይተው ለእኔ ሀብት ሆነው ተሰጥተዋልና። አሮንንና ልጆቹን በምስክሩ ድንኳን ፊት አቁማቸው፤ ክህነታቸውንም፥ በመሠዊያውና በመጋረጃው ውስጥ ያለውንም ሁሉ ይጠብቁ፤ ከሌላ ወገን የዳሰሰ ቢኖር ይገደል።”
ዘኍልቍ 3:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር፤ የአሮን ልጆች የበኵሩ ስም ናዳብ፣ የሌሎቹም አብዩድ አልዓዛርና ኢታምር ይባላል። እርሱ ለክህነት አገልግሎት የለያቸው፣ ካህናት ለመሆን የተቀቡት የአሮን ወንድ ልጆች ስም ይህ ነው፤ ናዳብና አብዩድ ግን በሲና ምድረ በዳ ባልተፈቀደ እሳት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ባቀረቡ ጊዜ እዚያው እፊቱ ወድቀው ሞቱ። ወንዶች ልጆች ስላልነበሯቸውም አልዓዛርና ኢታምር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን በክህነት ያገለግሉ ነበር። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የሌዊን ነገድ አምጥተህ ካህኑን አሮንን በአገልግሎቱ እንዲረዱት ከፊቱ አቁማቸው፤ በመገናኛው ድንኳን የማደሪያውን አገልግሎት በመፈጸም ለርሱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ የሚያስፈልጉትን ተግባሮች ያከናውኑ፤ የማደሪያውን ሥራ በመሥራትና የእስራኤላውያንን ግዴታ በመወጣት የመገናኛውን ድንኳን ሁሉ ይጠብቁ። ሌዋውያኑን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ተለይተው ለርሱ ፈጽመው የተሰጡ ናቸው። አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ እነርሱም ክህነታቸውን ይጠብቁ፤ ሌላ ሰው ማደሪያውን ቢቀርብ ግን ይገደል።”
ዘኍልቍ 3:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። የተቀቡ ካህናት በክህነትም ያገለግሉ ዘንድ የቀደሳቸው የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው። ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ እርሱንና ማኅበሩን ሁሉ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ነገር በመገናኛው ድንኳን ፊት ይጠብቁ። የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ፥ የእስራኤልን ልጆች ለማገልገል የሚያስፈልገውንም ነገር ይጠብቁ። ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ። አሮንንና ልጆቹን አቁማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ሌላ ሰውም ቢቀርብ ይገደል።
ዘኍልቍ 3:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር። አሮን አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኲሩ ናዳብ ሲሆን የቀሩት አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ነበሩ። እነዚህም በክህነት እንዲያገለግሉ ተቀብተው ነበር። ነገር ግን ከእነርሱ ውስጥ ናዳብና አቢሁ በሲና በረሓ በእግዚአብሔር ፊት ያልተቀደሰ እሳት ጭረው በማቅረባቸው ተቀሥፈው ሞቱ፤ እነርሱም ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህም አልዓዛርና ኢታማር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በክህነት ያገለግሉ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የሌዊን ነገድ አቅርበህ ለካህኑ አሮን አገልጋዮች እንዲሆኑ መድባቸው፤ እነርሱም አሮንንና መላውን ማኅበር በመገናኛው ድንኳን በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚገኙ መገልገያ ዕቃዎች ኀላፊዎች ይሆናሉ። እስራኤላውያንንም በድንኳኑ ውስጥ በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። ከእስራኤላውያን ሁሉ ተለይተው ለአሮንና ለልጆቹ ያገለግሉ ዘንድ ሌዋውያንን መድባቸው። የክህነቱንም ሥራ ያከናውኑ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ ከእነርሱ በቀር ሌላ ሰው ይህን ሥራ ለማከናወን ቢሞክር በሞት ይቀጣ።”
ዘኍልቍ 3:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። እነዚህ የአሮን ልጆች ስሞች ናቸው፤ በኩሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። የአሮን ልጆች፥ እርሱም በክህነት አገልግሎት እንዲያገለግሉ የቀደሳቸው፥ የተቀቡ ካህናት ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው። ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በጌታ ፊት ያልተፈቀደውን እሳት ባቀረቡ ጊዜ በጌታ ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የሌዊን ነገድ አምጥተህ አቅርብ እንዲያገለግሉትም በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። የማደሪያውንም ሥራ እየሠሩ፥ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለእርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ያለባቸውን ግዴታዎች ይፈጽሙ። የማደሪያውንም ሥራ እየሠሩ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቃሉ፥ ለእስራኤልንም ልጆች ያለባቸውን ግዴታ ይወጣሉ። ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች መካከል ለእርሱ ፈጽሞ የተሰጡ ናቸው። አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ማናቸውም ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል።”