ኦሪት ዘኊልቊ 13
13
የከነዓንን ምድር እንዲመረምሩ የተላኩ ሰላዮች
(ዘዳ. 1፥19-33)
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ከዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አንዳንድ የሕዝብ መሪዎችን መርጠህ፥ እኔ ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ወደ ከነዓን ምድር ሄደው የምድሪቱን ሁኔታ መርምረው እንዲመለሱ ላካቸው፤” 3ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ከእስራኤል መሪዎች መካከል ከፋራን ምድረ በዳ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ላከ። 4ስማቸው እንደሚከተለው ነበር፤ ከሮቤል ነገድ የዛኩር ልጅ ሻሙዓ፥ 5ከስምዖን ነገድ የሖሪ ልጅ ሣፋጥ፥ 6ከይሁዳ ነገድ የይፉኔ ልጅ ካሌብ፥ 7ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግአል፥ 8ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ ሆሼዓ 9ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፥ 10ከዛብሎን ነገድ የሶዲ ልጅ ጋዱኤል፥ 11ከዮሴፍ ነገድ (እርሱም ከምናሴ ነገድ) የሱሲ ልጅ ጋዲ፥ 12ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፥ 13ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፥ 14ከንፍታሌም ነገድ የዋፍሲ ልጅ ናሕቢ፥ 15ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ገኡኤል።
16እንግዲህ የአገሪቱን ሁኔታ አጥንተው እንዲመለሱ ሙሴ የላካቸው ሰዎች እነዚህ ነበሩ፤ የነዌን ልጅ ሆሼዓን “ኢያሱ” ብሎ ስሙን ለወጠው።
17ሙሴም ሲልካቸው እንዲህ አላቸው፦ “በኔጌብ በኩል አድርጋችሁ ወደ ተራራማው አገር ውጡ። 18አገሪቱ ምን እንደምትመስል፥ ምን ያኽል ሕዝብ እንደሚኖርባትና የሕዝቡም ብርታት ምን ያኽል እንደ ሆነ መርምሩ፤ 19ምድሪቱ መልካም ወይም መጥፎ እንደ ሆነች፥ ሕዝቡም የሚኖሩት ግልጥ በሆኑ መንደሮች ወይም በተመሸጉ ከተሞች እንደ ሆነ አጥኑ። 20አፈሩ ለም፥ ምድሪቱም በደን የተሸፈነች መሆንዋን መርምሩ፤ አይዞአችሁ እዚያ ከሚገኘው ፍራፍሬ ይዛችሁ ኑ።” ወቅቱም የወይን ፍሬ መብሰል የጀመረበት ጊዜ ነበር።
21ስለዚህ ሰዎቹ ወደ ሰሜን ሄዱ፤ በአገሪቱም ከሚገኘው ከጺን ምድረ በዳ ጀምረው ለሐማት መተላለፊያ ቅርብ እስከሆነው ረሖብ ድረስ አጠኑ። 22በመጀመሪያው ወደ ኔጌብ ሄደው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ይህችም ኬብሮን “ዐናቂም” ተብለው የሚጠሩ የግዙፋን ሰዎች ዘር የሆኑ አሒማን፥ ሼሻይ እና ታልማይ የሚባሉት ጐሣዎች መኖሪያ ነበረች። (ኬብሮን የተመሠረተችውም በግብጽ ምድር ጾዓን ተብላ የምትጠራው ከተማ ከመቈርቈርዋ ሰባት ዓመት ቀደም ብሎ ነበር።) 23አልፈውም ወደ ኤሾኮል ሸለቆ ደረሱ፤ ከዚያም የወይን ዘለላ ያለበትን ቅርንጫፍ ቈረጡ፤ ያንንም የወይን ዘለላ አንድ ሰው ብቻውን ሊሸከመው የማይችል ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ሁለት ሰዎች በመሎጊያ በትከሻቸው ላይ ተሸከሙት፤ ከዚህም ጋር የሮማንና የበለስ ፍሬ ይዘው መጡ። 24ያ ቦታ “የኤሽኮል ሸለቆ” ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት እስራኤላውያን የወይን ፍሬ ዘለላ ቈርጠው ያመጡበት ስፍራ ስለ ነበር ነው። #13፥24 ኤሽኮል በዕብራይስጥ የወይን ፍሬ ዘለላ ማለት ነው።
25ሰዎቹ ምድሪቱን ለአርባ ቀኖች ካጠኑ በኋላ ተመለሱ። 26በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወደነበሩት ወደ ሙሴና አሮን ወደ መላውም የእስራኤል ማኅበር መጡ፤ እነርሱም ያዩትን ነገር ሁሉ አስረዱ፤ ያመጡትንም ፍሬ አሳዩአቸው፤ 27ለሙሴም እንዲህ ብለው ነገሩት፦ “ምድሪቱን አጥንተን በእርግጥም በማርና በወተት የበለጸገች አገር መሆንዋን ተረድተናል፤ ምድሪቱም የምታፈራው ፍሬ ዐይነት ይህ ነው፤ 28ነገር ግን በዚያች ምድር የሚኖሩ ሕዝብ እጅግ ብርቱዎች ናቸው፤ ከተሞቻቸውም ታላላቆችና የተመሸጉ ናቸው፤ ከዚህም ሁሉ በላይ እጅግ ግዙፋን የዐናቅ ዘሮች አይተናል። 29ዐማሌቃውያን በኔጌብ ምድር የሚኖሩ ሲሆን፥ ሒታውያን፥ ኢያቡሳውያንና አሞራውያን በተራራማው አገር፥ ከነዓናውያን ደግሞ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርና በሜዲቴራኒያን በባሕር ዳር ይኖራሉ።”
30ካሌብ ግን በሙሴ ፊት ሕዝቡን ጸጥ በማሰኘት “እነርሱን ድል ለመንሣት የሚያስችል በቂ ኀይል ስለ አለን አገሪቱን አሁኑኑ ሄደን እንያዛት አለ።”
31ከካሌብ ጋር ሄደው የነበሩት ሰዎች ግን “እኛ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ከቶ ኀይል የለንም፤ በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ከእኛ ይበልጥ ብርቱዎች ናቸው” ብለው ተናገሩ። 32ሊሰልሉ ስለ ሄዱበት አገርም ለእስራኤላውያን ያቀረቡት ዘገባ ተስፋ አስቈራጭ ነበር፥ እነርሱም፥ “ልንሰልል የሄድንበት አገር ወደ እርስዋ ለመኖር የሚመጣውን ሰው የምትውጥ ናት፤ እዚያ ያየናቸው ሰዎች ረጃጅሞች ናቸው። 33በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን የዐናቅን ዘሮች አይተናል፤ እኛ በእነርሱ ፊት ልክ እንደ ፌንጣ ያኽል ሆነን ነበር የታየነው፤ እነርሱም እንደዚያው አድርገው ሳይመለከቱን አይቀሩም” አሉ። #ዘፍ. 6፥4።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 13: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997