የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 12

12
ማርያምና አሮን ሙሴን እንደ ተቃወሙ
1ሙሴ ከኩሽ ነገድ የሆነች (ኢትዮጵያዊት) ሴት በማግባቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በሐሜት እንዲህ ሲሉ ነቀፉት፦ 2“እግዚአብሔር የተናገረው በሙሴ አማካይነት ብቻ ነውን? በእኛስ አማካይነት ተናግሮ የለምን?” እግዚአብሔርም እነርሱ የተናገሩትን ሁሉ ሰማ። 3(በመሠረቱ ሙሴ በምድር ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ትሑት ሰው ነበር።)
4በድንገትም እግዚአብሔር ሙሴን፥ አሮንንና ማርያምን “እናንተ ሦስታችሁ ወደ መገናኛው ድንኳን ኑ!” አላቸው፤ እነርሱም ሄዱ፤ 5እግዚአብሔርም በደመና ዐምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ በመቆም “አሮን! ማርያም!” ብሎ ጠራቸው፤ ሁለቱም ወደ ፊት ቀረቡ፤ 6እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ እኔ የምነግራችሁን አድምጡ! በመካከላችሁ ነቢያት ቢኖሩ ራሴን የምገልጥላቸው በራእይ ነው፤ በሕልምም አነጋግራቸዋለሁ፤ 7ከአገልጋዬ ከሙሴ ጋር የምነጋገረው ግን እንደዚያ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው፤ #12፥7 እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው፦ ወይም “እኔ እርሱን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ኀላፊ አድርጌ ሾሜዋለሁ።” #ዕብ. 3፥2። 8ስለዚህም እኔ ከእርሱ ጋር ቃል ለቃል በግልጥ እነጋገራለሁ እንጂ ስውር በሆነ አነጋገር አልናገረውም፤ የእኔን የእግዚአብሔርን መልክ ያያል፤ ታዲያ፥ እናንተ በአገልጋዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ እንዴት ደፈራችሁ?”
9እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጥቶ ሄደ። 10ደመናው ከድንኳኑ ላይ በተነሣ፤ ጊዜ ማርያም ለምጻም ሆነች፤ ለምጹም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፤ አሮን ወደ ማርያም በተመለከተ ጊዜ ለምጻም ሆና አያት። 11አሮንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ሆይ፥ በስንፍናችን ስለ ሠራነው ኃጢአት ይህ አሠቃቂ ቅጣት እንዲፈጸምብን አታድርግ፤ 12እርስዋንም በእናቱ ማሕፀን ሳለ ሞቶ ግማሽ አካሉ ከተበላ በኋላ እንደ ተወለደ ጭንጋፍ እንድትመስል አታድርግ።” 13ስለዚህ ሙሴ “እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ ፈውሳት” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
14እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ላይ ቢተፋባት እንኳ ኀፍረትዋን ተሸክማ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ትቈይ የለምን? ስለዚህም እርስዋ ከሰፈር ወጥታ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በገለልተኛ ቦታ ትቈይ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሳ ወደ ሰፈር ልትገባ ትችላለች።” #ዘኍ. 5፥2-3። 15ከዚያም በኋላ ማርያም ከሰፈር ወጥታ ለብቻዋ ተዘግቶባት ቈየች፤ እርስዋ እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ ከሰፈር አልተንቀሳቀሱም። 16ከዚያም በኋላ ከሐጼሮት ተነሥተው በፋራን ምድረ በዳ ሰፈሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ