የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 1

1
የመጀመሪያው የእስራኤል የሕዝብ ቈጠራ
1እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፥ ሁለተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን በሲና በረሓ ሳሉ፥ እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን እንዲህ ሲል አነጋገረው፦ 2-3“አንተና አሮን፥ የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ በየነገዱና በየቤተሰቡ ኻያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነውን እያንዳንዱን ወንድ አንድ በአንድ እየቈጠራችሁ መዝግቡ። 4ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ የቤተሰብ አለቃ ከእናንተ ጋር ይሁን። 5የሚረዱአችሁ ሰዎች ስም የሚከተሉት ናቸው፦
ከሮቤል
የሸዴኡር ልጅ ኤሊጹር
6ከስምዖን
የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል
7ከይሁዳ
የዓሚናዳብ ልጅ ነአሶን
8ከይሳኮር
የጹዓር ልጅ ናትናኤል
9ከዛብሎን
የሔሎን ልጅ ኤሊአብ
10ከዮሴፍ ልጆች፦
ከኤፍሬም
የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሻማዕ
ከምናሴ
የጴዳጹር ልጅ ገማልኤል
11ከብንያም
የጊድዖኒ ልጅ አቢዳን
12ከዳን
የዓሚሻዳይ ልጅ አሒዔዜር
13ከአሴር
የዖክራን ልጅ ፋግዒኤል
14ከጋድ
የደዑኤል ልጅ ኤልያሳፍ
15ከንፍታሌም
የዔናን ልጅ አሒራዕ።”
16ከማኅበሩ መካከል፥ ከየነገዶቻቸው የእስራኤል ቤተሰብ መሪዎች ሆነው የተመረጡት እነዚህ ነበሩ።
17ሙሴና አሮን እነዚህን ስሞቻቸው የተጠቀሱትን ሰዎች ወሰዱ፤ 18ሁለተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን፥ ማኅበሩን ሁሉ በአንድነት ሰብስበው በየነገዱና በየቤተሰቡ ከመደቡ በኋላ የሕዝብ ቈጠራ አደረጉ፤ ዕድሜአቸው ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ስማቸው እየተመዘገበ ተቈጠሩ። 19በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በሲና በረሓ ሕዝቡን ቈጠረ። 20ወታደር ሆነው ለማገልገል ችሎታ ያላቸው፥ ዕድሜአቸው ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነ ወንዶች ከያዕቆብ ልጆች በኲር ከሆነው ከሮቤል ነገድ 21ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩት አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
22ከስምዖን ነገድ በየትውልዳቸው በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው፥ እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነው ወደ ጦርነት ለመውጣት የሚችል ወንድ ሁሉ በየራሳቸው የተቈጠሩት፥ 23ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 24ከጋድ ነገድ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ የተቈጠሩት፤ 25አርባ አምስት ሺህ ስድስት ሞቶ ኀምሳ ነበሩ።
26-27ከይሁዳ ነገድ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው፥ እንደየስማቸው ቊጥር፥ ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 28የይሳኮር ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 29ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
30የዛብሎን ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 31ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 32ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 33ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤
34የምናሴ ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 35ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
36የብንያም ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 37ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 38የዳን ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 39ከዳን ነገድ የተቈጠሩ ሥልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 40የአሴር ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 41ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
42የንፍታሌም ልጆች፥ በየትውልዳቸው በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 43ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
44እያንዳንዱ የራሱን ወገን ወክሎ በመምጣት በዐሥራ ሁለቱ የነገድ መሪዎች ርዳታ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው እነዚህ ናቸው፤ 45በዚህም መሠረት መላው እስራኤላውያን በየነገዳቸው፥ ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑት ወደ ጦርነት ለመሄድ የሚችሉ ሁሉ፥ 46በጠቅላላ የተቈጠሩት ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። #ዘኍ. 26፥1-51።
47ሌዋውያን ግን ከሌሎች ነገዶች ጋር አብረው አልተቈጠሩም። 48እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎት ነበር፤ 49“እስራኤላውያን ወንዶችን ስትቈጥር፥ የሌዊን ነገድ አትጨምር። 50በዚህ ፈንታ ሌዋውያንን በመገናኛው ድንኳንና በውስጡም ባሉት የመገልገያ ዕቃዎች ላይ ኀላፊዎች አድርገህ መድባቸው፤ እነርሱ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ይሸከማሉ፤ በድንኳኑም ውስጥ ያገለግላሉ፤ በዙሪያውም ይሰፍራሉ። 51ሰፈራችሁን ለቃችሁ በምትሄዱበት ጊዜ ሌዋውያን ብቻ ድንኳኑን ነቅለው በሚሰፍሩበት አዲስ ቦታ ይተክሉታል፤ ከእነርሱ በቀር ወደ ድንኳኑ የሚቀርብ ማንኛውም ሰው በሞት ይቀጣል። 52ሌሎቹ እስራኤላውያን በየቡድናቸውና በየሰፈራቸው ድንኳኖቻቸውን ይተክላሉ። 53ነገር ግን ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ በመቅረብ ቊጣዬን አነሣሥቶ የእስራኤልን ማኅበር እንዳያስፈጅ ሌዋውያን በድንኳኑ ዙሪያ ሰፍረው ይጠብቁት።” 54ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉን ነገር አደረጉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}