መጽሐፈ ነህምያ 5:1-19

መጽሐፈ ነህምያ 5:1-19 አማ05

በአንድ ወቅት ወንዶችና ሴቶች ወገኖቻቸው በሆኑ የአይሁድ አለቆቻቸው ላይ ከባድ አቤቱታ አሰሙ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ “ብዙ ቤተሰብ ስላለን ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችለን እህል እንፈልጋለን” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ “ከደረሰብን ብርቱ ራብ ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችል እህል ለማግኘት ስንል እርሻችንን፥ የወይን ተክላችንንና ቤታችንን ሁሉ መያዣ አድርገን እስከ መስጠት ደርሰናል” ይሉ ነበር። ሌሎችም ደግሞ “ስለ እርሻችንና ስለ ወይን ተክላችን መንግሥት የጠየቀንን ግብር ለመክፈል የገንዘብ ብድር ተበድረናል፤ ከአይሁድ ወገኖቻችን ጋር ዘራችን አንድ ነው፤ የእኛ ልጆች ከእነርሱ ልጆች የሚለዩበት ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ የገዛ ልጆቻችንን ለባርነት አሳልፈን ለመስጠት ተገደናል፤ እንዲያውም ከሴቶች ልጆቻችን አንዳንዶቹ ባሪያዎች ሆነዋል፤ ነገር ግን እርሻችንና የወይን ተክል ቦታችን ስለ ተወሰዱ ኀይል የሌለን ሆነናል” በማለት አቤቱታ አሰሙ። እኔም አቤቱታቸውን በሰማሁ ጊዜ ተቈጣሁ፤ ላደርገው የሚገባኝንም በልቤ ወስኜ የሕዝቡ መሪዎች የሆኑትን ባለሥልጣኖች “እናንተ እኮ የገዛ ወንድሞቻችሁን በመጨቈን አራጣ ታስከፍላላችሁ!” በማለት በቊጣ ገሠጽኳቸው። ለችግሩም መፍትሔ ለማግኘት ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቤ “ለአሕዛብ ሕዝቦች የተሸጡ አይሁድ ወገኖቻችንን ራሳችን ልንቤዣቸው በማሰብ የሚቻለንን ሁሉ አደረግን፤ እናንተ ደግሞ እነሆ፥ የገዛ ወንድሞቻችሁ የሆኑት አይሁድን ወገኖቻቸው ለሆናችሁት ለእናንተ ባርያዎች አድርገው ራሳቸውን እንዲሸጡላችሁ በማድረግ ላይ ትገኛላችሁ!” ብዬ ገሠጽኳቸው፤ መሪዎቹም የሚመልሱት ቃል አጥተው ዝም አሉ። እኔ ግን ንግግሬን በመቀጠል እንዲህ አልኳቸው፤ “ያደረጋችኹት ነገር ትክክል አይደለም! እግዚአብሔርን መፍራትና ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ ይህን አድርጋችሁ ቢሆን ኖሮ፥ አሕዛብ ጠላቶቻችን ባልተዘባበቱብንም ነበር። ሕዝቡ ከእኔ ገንዘብም ሆነ እህል እንዲበደሩ ፈቅጄላቸዋለሁ፤ የሥራ ባልደረቦቼና የእኔ አገልጋዮች የሆኑት ሁሉ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ ፈቅጃለሁ፤ እንግዲህስ ‘የተበደራችሁትን ዕዳ ክፈሉን’ ብለን መጠየቅ ይቅርብን፤ ገንዘብም ሆነ እህል ወይም ወይንና የወይራ ዘይት ቢሆን ያበደራችሁትን ሁሉ ወለዱን ተዉላቸው፤ እርሻቸውን የወይንና የወይራ ዘይት ተክላቸውንና ቤታቸውን ሁሉ አሁኑኑ መልሱላቸው።” መሪዎቹም “እንዳዘዝከን እናደርጋለን፤ የተወሰደባቸውን ሀብትና ንብረት ሁሉ እንመልስላቸዋለን፤ የተበደሩትንም ዕዳ ክፈሉ ብለን አንጠይቃቸውም” ሲሉ መለሱልኝ። እኔም ካህናቱን ወደ ውስጥ ጠርቼ፥ መሪዎቹ የገቡትን ቃል ይፈጽሙ ዘንድ እንዲያስምሉአቸው አደረግሁ። ለብሼው የነበረውንም ልብስ በማውለቅ አራግፌ “ከእናንተ መካከል ማንም ሰው የገባውን የተስፋ ቃል ቢያፈርስ እግዚአብሔር እንደዚህ ያድርገው፤ ቤት ንብረቱንም ወስዶ ባዶ እጁን ያስቀረው” አልኳቸው። በዚያም የተገኘው ሰው ሁሉ በአንድ ድምፅ “አሜን!” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ መሪዎቹም የገቡትን ቃል ፈጸሙ። አርጤክስስ ንጉሠ ነገሥት ከሆነበት ከኻኛው ዓመት ጀምሮ ሠላሳ ሁለት ዓመት እስከ ሆነው ድረስ እኔ የይሁዳ ገዢ በሆንኩበት የዐሥራ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘመዶቼም ሆኑ ወይም እኔ ራሴ ለአንድ አገረ ገዢ የሚገባውን ምግብ አልበላንም። ከእኔ በፊት የሕዝብ ገዢ ሆኖ የተሾመው ሁሉ በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም በመሆን፥ በየቀኑ ለምግብና ለመጠጥ የሚሆን አርባ ብር ያስከፍላቸው ነበር፤ የገዢዎቹም አገልጋዮች እንኳ በሕዝቡ ላይ ሠልጥነውባቸው ይጨቊኑአቸው ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንደዚያ አላደረግሁም። ያለኝን ኀይል ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጽር እንደገና በማሳነጽ ተግባር ላይ አዋልኩት እንጂ ለግሌ ምንም ዐይነት ንብረት አልሰበሰብኩም፤ አገልጋዮቼም ሁሉ በዚህ ሥራ ተባበሩኝ፤ ከአካባቢ አገሮች ወደ እኔ ከመጡት ሕዝቦች ሌላ በየዕለቱ ከእኔ ጋር የሚመገቡ አይሁድና የመሪዎቻቸው ቊጥር አንድ መቶ ኀምሳ ነበር። በየዕለቱ አንድ በሬ፥ ስድስት ምርጥ በጎችና ብዙ ዶሮች ታርደው ይዘጋጁልኝ ነበር፤ በተጨማሪም በየዐሥር ቀን አንድ ጊዜ የወይን ጠጅ ግብዣ አደርግላቸው ነበር፤ ነገር ግን በሕዝቡ ላይ የተጣለውን ከባድ ሸክም ስለማውቅ፥ ለአገረ ገዢነት የሚገባውን አበል አልጠየቅሁም። አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያደረግኹትን ቅንነት ሁሉ በማሰብ ቸርነት አድርግልኝ።