መጽሐፈ ነህምያ 4:6-14

መጽሐፈ ነህምያ 4:6-14 አማ05

እኛም ቅጽሩን መልሶ የማነጹን ሥራ ቀጠልን፤ ሕዝቡ በትጋት በመሥራቱ ሥራው እየተፋጠነ ሄዶ ግማሽ ደረሰ። ሰንባላጥ፥ ጦቢያና የዐረብ፥ የዐሞን፥ የአሽዶድም ሕዝብ ጭምር የኢየሩሳሌምን ቅጽር ግንብ እንደገና መልሰን በመሥራት ረገድ ጥሩ የሥራ ውጤት ማስገኘታችንንና በቅጽሮቹ መካከል የነበሩት ክፍት ቦታዎች መዘጋታቸውን በሰሙ ጊዜ በብርቱ ተቈጡ፤ ስለዚህም በአንድነት ተባብረው ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣትና አደጋ ጥለው ሽብር ለመፍጠር በእኛ ላይ አድማ አደረጉ፤ እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ እነርሱንም ለመቋቋም ሌሊትና ቀን ቆመው የሚጠብቁ ዘበኞችን መደብን። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች “የሸክም ሥራ እያደከመን ሄደ፤ ገና መነሣት ያለበት ፍርስራሽ ብዙ ነው፤ ቅጽሩን እንሠራ ዘንድ አንችልም” አሉ። “ጠላቶቻችን የምናደርገውን ከማወቃቸውና ከማየታቸው በፊት በመካከላቸው ተገኝተን እነርሱን ገድለን ሥራቸውንም እናቆመዋለን” አሉ። በጠላቶቻችን መካከል የሚኖሩ አይሁድ ወደ ከተማው እየመጡ ጠላቶቻችን እኛን ለማጥቃት ያቀዱ መሆናቸውን ደጋግመው በማስጠንቀቅ ነገሩን። ስለዚህም ከሕዝባችን መካከል ሰይፍ፥ ጦርና ቀስት የያዙ ሰዎችን በየጐሣቸው በማዘጋጀት፥ ሥራው ባልተጠናቀቀበት ቦታ ሁሉ በቅጽሩ ግንብ በስተጀርባ እንዲመሸጉ አደረግሁ። ሕዝቡ ተጨንቀው ስላየሁ፥ እነርሱንና መሪዎቻቸውን፥ ሌሎችንም ባለሥልጣኖች ሁሉ “ከጠላቶቻችን የተነሣ አትፍሩ፤ ምን ያኽል ታላቅና ግርማው የሚያስፈራ አምላክ እንዳለንና እርሱ ስለ ወገኖቻችሁ፥ ስለ ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ ስለ ቤት ንብረታችሁም እንደሚዋጋላችሁ አስታውሱ” አልኳቸው።