የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 4

4
ነህምያ የገጠመውን የሥራ ተቃውሞ ሁሉ መቋቋሙ
1እኛ አይሁድ የቅጽሩን ግንብ ሥራ መጀመራችንን ሰንባላጥ በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ ተበሳጭቶም ሊዘባበትብን ተነሣ። 2በጓደኞቹና በሰማርያ ወታደሮች ፊት “እነዚህ ደካሞች አይሁድ ምን ለማድረግ አስበዋል? ከተማይቱን እንደገና መልሰው ለመሥራት ዐቅደዋልን? መሥዋዕት በማቅረብስ ሥራውን በአንድ ቀን ለመፈጸም የሚችሉ ይመስላቸዋልን? ለግንብ የሚሆኑ ድንጋዮችንስ ከተቃጠለው ፍርስራሽ ክምር ውስጥ ማውጣት ይችሉ ይሆን?” ሲል በመዘበት ተናገረ።
3በአጠገቡም ቆሞ የነበረው ጦቢያ በበኩሉ፦ “እነርሱ ምን ዐይነት ቅጽር መሥራት ይችላሉ? የእነርሱ ግንብ ቀበሮ እንኳ ብትወጣበት ሊፈርስ ይችላል!” ሲል በማፌዝ ተናገረ።
4እኔም እንዲህ ስል ጸለይሁ፤ “አምላክ ሆይ! እንዴት እንደሚሳለቁብን ተመልከት፤ ይህም ስድባቸው በራሳቸው ላይ ይምጣባቸው፤ ያላቸውን ሀብት ሁሉ ተገፈው በባዕድ አገር ስደተኞች ይሁኑ፤ 5ስለሚያደርጉት ክፉ ነገር ምሕረት አታድርግላቸው፤ የፈረሰውን በመሥራታችን በስድብ አዋርደውናልና በደላቸውን አትርሳ።”
6እኛም ቅጽሩን መልሶ የማነጹን ሥራ ቀጠልን፤ ሕዝቡ በትጋት በመሥራቱ ሥራው እየተፋጠነ ሄዶ ግማሽ ደረሰ።
7ሰንባላጥ፥ ጦቢያና የዐረብ፥ የዐሞን፥ የአሽዶድም ሕዝብ ጭምር የኢየሩሳሌምን ቅጽር ግንብ እንደገና መልሰን በመሥራት ረገድ ጥሩ የሥራ ውጤት ማስገኘታችንንና በቅጽሮቹ መካከል የነበሩት ክፍት ቦታዎች መዘጋታቸውን በሰሙ ጊዜ በብርቱ ተቈጡ፤ 8ስለዚህም በአንድነት ተባብረው ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣትና አደጋ ጥለው ሽብር ለመፍጠር በእኛ ላይ አድማ አደረጉ፤ 9እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ እነርሱንም ለመቋቋም ሌሊትና ቀን ቆመው የሚጠብቁ ዘበኞችን መደብን።
10በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች
“የሸክም ሥራ እያደከመን ሄደ፤
ገና መነሣት ያለበት ፍርስራሽ ብዙ ነው፤
ቅጽሩን እንሠራ ዘንድ አንችልም” አሉ።
11“ጠላቶቻችን የምናደርገውን ከማወቃቸውና ከማየታቸው በፊት በመካከላቸው ተገኝተን እነርሱን ገድለን ሥራቸውንም እናቆመዋለን” አሉ። 12በጠላቶቻችን መካከል የሚኖሩ አይሁድ ወደ ከተማው እየመጡ ጠላቶቻችን እኛን ለማጥቃት ያቀዱ መሆናቸውን ደጋግመው በማስጠንቀቅ ነገሩን። 13ስለዚህም ከሕዝባችን መካከል ሰይፍ፥ ጦርና ቀስት የያዙ ሰዎችን በየጐሣቸው በማዘጋጀት፥ ሥራው ባልተጠናቀቀበት ቦታ ሁሉ በቅጽሩ ግንብ በስተጀርባ እንዲመሸጉ አደረግሁ።
14ሕዝቡ ተጨንቀው ስላየሁ፥ እነርሱንና መሪዎቻቸውን፥ ሌሎችንም ባለሥልጣኖች ሁሉ “ከጠላቶቻችን የተነሣ አትፍሩ፤ ምን ያኽል ታላቅና ግርማው የሚያስፈራ አምላክ እንዳለንና እርሱ ስለ ወገኖቻችሁ፥ ስለ ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ ስለ ቤት ንብረታችሁም እንደሚዋጋላችሁ አስታውሱ” አልኳቸው። 15ጠላቶቻችንም የተማማሉበትን አድማ የደረስንበት መሆኑን ሰሙ፤ እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን እንዳከሸፈባቸው ተገነዘቡ፤ ከዚያ በኋላ ሁላችንም የቅጽሩን ግንብ መሥራታችንን ቀጠልን።
16ከዚህም ጊዜ ጀምሮ እኔ ያሰለፍኳቸው ሰዎች እኩሌቶቹ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ ጥሩር ለብሰው፥ ጦር ይዘው፥ ጋሻ አንግበው፥ ቀስት ደግነው ዘብ በመቆም እንዲጠብቁ አደረግሁ፤ መሪዎቻችንም ለሕዝቡ ሙሉ ድጋፍ ይሰጡ ነበር፤ 17ቅጽሩን የሚሠሩትን ሁሉ ያበረታቱ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ፥ ተሸካሚዎቹ ጭምር በአንድ እጃቸው ሲሠሩ፥ በሌላ እጃቸው የጦር መሣሪያ ይዘው ለመከላከል ዝግጁዎች ነበሩ። 18እያንዳንዱም ግንበኛ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ እምቢልታ ነፊውም ከአጠገቤ አይለይም ነበር። 19ሕዝቡን፥ መሪዎቻቸውንና ሹማምንቱን “የቅጽሩ ሥራ ታላቅና እጅግ ሰፊ ስለ ሆነ፥ እርስ በርሳችን በመራራቃችን አንዱ ከሌላው ጋር ለመገናኘት አይችልም። 20የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ወደ እኔ መጥታችሁ በዙሪያዬ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋልናል” አልኳቸው፤ 21ስለዚህም በየቀኑ ከማለዳ ጀምሮ በምሽት፥ ከዋክብት እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ እኩሌቶቹ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ መሣሪያ ታጥቀው ዘብ በመቆም ይጠብቁ ነበር።
22በዚህን ጊዜ የሥራ ኀላፊዎቹን “በሌሊት ከተማይቱን ለመጠበቅ፥ ቀን ሥራችንን ያለ ሥጋት ለመሥራት እንችል ዘንድ እናንተም ሆናችሁ ረዳቶቻችሁ፥ ሌሊት ሌሊት በኢየሩሳሌም ቈዩ” አልኳቸው። 23እኔም ሆንኩ የሥራ ጓደኞቼ፥ አገልጋዮቼም ሆኑ የክብር ዘቦቼ፥ ሁላችንም ሌሊት እንኳ ልብሳችንን አናወልቅም ነበር። በዚህም ዐይነት ውሃ ስንቀዳ እንኳ መሣሪያችን ከእጃችን አልተለየም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ