መጽሐፈ ነህምያ 13:1-31

መጽሐፈ ነህምያ 13:1-31 አማ05

የኦሪት ሕግ ከፍ ባለ ድምፅ በተነበበላቸው ጊዜ ሰዎቹ ሲያዳምጡ “ሞአባውያንና ዐሞናውያን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ለዘለዓለም አይቀላቀሉ” ከሚለው አንቀጽ ደረሱ። ይህም ትእዛዝ የተሰጠበት ምክንያት እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር በወጡበት ጊዜ በጒዞ ላይ ሳሉ ሞአባውያንና ዐሞናውያን ምግብና ውሃ ስለ ከለከሉአቸው ነበር፤ ይልቁንም ይህን በማድረግ ፈንታ ለበለዓም ገንዘብ ሰጥተው የእስራኤልን ሕዝብ እንዲረግምላቸው አድርገው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን መርገሙን ወደ በረከት ለወጠው። ይህም ሕግ ሲነበብ እስራኤላውያን በሰሙት ጊዜ ባዕዳን የሆኑ ሕዝቦችን ከመካከላቸው አስወገዱ። የቤተ መቅደስ ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ የሆነው ካህኑ ኤልያሺብ ለረጅም ጊዜ ከጦቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው፤ ከዚህም የተነሣ የእህል መባ፥ ዕጣን፥ የቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት፥ ከእህል፥ ከወይን ጠጅ፥ ከወይራ ዘይት ተውጣጥቶ ለሌዋውያኑ ለቤተ መቅደስ መዘምራንና ለዘብ ጠባቂዎች የሚሰጠው ዐሥራትና ለካህናቱ የሚሰጥ መባ ሁሉ እንዲቀመጥበት ታስቦ በተለይ የተሠራውን ታላቅ ክፍል ጦቢያ በመኖሪያነት ይጠቀምበት ዘንድ ኤልያሺብ ፈቅዶለት ነበር። ይህም ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርኩም፤ አርጤክስስ የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት በሆነ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ባቢሎን ተመልሼ ሄጄ ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከንጉሡ ፈቃድ ጠይቄ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስኩ፤ እዚያም እንደ ደረስኩ ኤልያሺብ ለጦቢያ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ አንድ መኖሪያ ክፍል የፈቀደለት መሆኑን ሰማሁ፤ በቊጣ ተነሥቼ የጦቢያን ንብረት ሁሉ ከክፍሉ በማስወጣት አሽቀንጥሬ ጣልኩ፤ ክፍሎቹም በሕጉ መሠረት በሥርዓት እንዲነጹና የቤተ መቅደሱም ንዋያተ ቅድሳት፥ የእህል መባውና ዕጣኑ ወደዚያ ተመልሰው እንዲገቡ ትእዛዝ ሰጠሁ። እንዲሁም አገልግሎቱን የሚፈጽሙት የቤተ መቅደሱ መዘምራንና ሌሎችም ሌዋውያን ኢየሩሳሌምን ለቀው በመውጣት ወደየእርሻቸው ተመልሰው መግባታቸውን ተገነዘብኩ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሕዝቡ ለመዘምራኑና ለሌዋውያኑ በቂ መተዳደሪያ ባለመስጠታቸው ነበር። ቤተ መቅደሱም ይህን ያኽል ቸል እስኪባል ዝም ብለው በመመልከታቸው ባለሥልጣኖችን ገሠጽኩ፤ ሌዋውያኑንና መዘምራኑንም ወደ ቤተ መቅደስ መልሼ በማምጣት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አደረግሁ፤ ከዚህም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ እንደገና ከእህልና ከወይን ጠጅ፥ ከወይራ ዘይትም የሚፈለግባቸውን ከዐሥር አንድ እያወጡ ወደ ቤተ መቅደስ ዕቃ ግምጃ ቤት ማምጣት ጀመሩ። ለዕቃ ግምጃ ቤቱም ኀላፊነት ካህኑን ሼሌምያን፥ የሕግ ምሁሩን ሳዶቅንና ሌዋዊውን ፐዳያን መደብሁ፤ የማታንያ የልጅ ልጅ የሆነው የዛኩር ልጅ ሐናንም የእነርሱ ረዳት ነበር፤ እነዚህም ሰዎች ለሥራ ጓደኞቻቸው የሚሆነውን መተዳደሪያ ለማከፋፈል ታማኞች ነበሩ። አምላኬ ሆይ፥ ለቤተ መቅደስህና ለአገልግሎቱ መቃናት ስል እነዚህን ሁሉ በታማኝነት ማድረጌን በማሰብ ቸርነት አድርግልኝ። በእነዚያም ቀኖች በይሁዳ በሰንበት ቀን ወይን የሚጨምቁ፥ እህልን፥ ወይን ጠጅን፥ የወይን ዘለላን፥ በለስን፥ ሌሎችንም ነገሮች ሁሉ በአህያ የሚጭኑ መሆናቸውን አየሁ፤ እነዚህንም ሁሉ በሰንበት ቀን ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው እንዳይሸጡ አስጠነቀቅኋቸው። ከዚህም ጋር በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የጢሮስ ተወላጆች ዓሣና ሌሎች ሸቀጦችን በየዐይነቱ በሰንበት ቀን ወደ ከተማይቱ እያስገቡ ለይሁዳ ሕዝብ ይሸጡ ነበር፤ እኔም የአይሁድ መሪዎችን በመገሠጽ እንዲህ አልኳቸው፥ “የምታደርጉትን ክፉ ነገር ሁሉ ተመልከቱ! እነሆ ሰንበትን እያረከሳችኋት ነው፤ አምላካችን በእኛና በከተማይቱ ላይ ይህን ጥፋት ያመጣው የቀድሞ አባቶቻችሁ ይህን ጥፋት ስላደረጉ አይደለምን? አሁንም እናንተ ሰንበትን ባለማክበራችሁ የእግዚአብሔርን ቊጣ በእስራኤል ላይ ታነሣሣላችሁ።” ከዚህም በኋላ በሰንበት ዋዜማ መሸትሸት ሲል የከተማይቱ ቅጽር በሮች እንዲዘጉና የሰንበት ቀን ከማለፉም በፊት እንዳይከፈቱ ትእዛዝ ሰጠሁ፤ በሰንበት ቀን ወደ ከተማይቱ ምንም ሸክም እንዳይገባ ይቈጣጠሩ ዘንድ ከአገልጋዮቼ አንዳንዶቹን በቅጽር በሮች አሰማራሁ። በየዐይነቱ ሸቀጣሸቀጦችን ለሺያጭ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ለአንድ ጊዜም ለሁለት ጊዜም የሰንበት ዋዜማ የሆነውን የዓርብን ምሽት ከከተማይቱ ቅጽር ውጪ አሳለፉ፤ እኔም “ማለድ ብላችሁ ለመግባት በማሰብ በዚያ ማደራችሁ ጥቅም የለውም፤ እንዲህ ማድረጋችሁን የምትቀጥሉ ከሆነ በእናንተ ላይ የኀይል እርምጃ ለመውሰድ እገደዳለሁ” ብዬ አስጠነቀቅኋቸው፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ በሰንበት ቀን መምጣታቸውን አቆሙ። ሌዋውያኑም በሕጉ መሠረት ራሳቸውን አንጽተው የሰንበት ቀን በቅድስና የተጠበቀች መሆንዋን ለማረጋገጥ የቅጽር በሮቹን እንዲቈጣጠሩ አዘዝኳቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ስለዚህም ሁሉ እንድታስበኝና ስለ ጽኑ ፍቅርህም እንድትታደገኝ እለምንሃለሁ። በዚያው ወራት ደግሞ ከአይሁድ ሕዝብ ብዙዎቹ የአሽዶድ፥ የዐሞንና የሞአብ አገር ሴቶችን ማግባታቸውን ተገነዘብኩ፤ እኩሌቶች ልጆቻቸው የአሽዶድንና የሌሎችንም አንዳንድንም ቋንቋዎች ይናገሩ ነበር፤ የአይሁድን ቋንቋ መናገር ተስኖአቸው ነበር። እነዚህንም ሰዎች ገሠጽኳቸው፤ ረገምኳቸውም፤ ደብድቤም ጠጒራቸውን ነጨሁ፤ ከዚህም በኋላ እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው ከባዕዳን ሕዝብ ጋር ጋብቻ እንዳይፈጽሙ በእግዚአብሔር ስም አስማልኳቸው። እንዲህም አልኳቸው፦ “የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ኃጢአት የሠራው በእንደዚህ ያለ ጋብቻ አይደለምን? ከብዙ ሕዝቦች መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም። እግዚአብሔርም ወዶት በሕዝቡ በእስራኤል ላይ አነገሠው፤ እርሱ ግን በባዕዳን ሴቶች አማካይነት ኃጢአት ሠራ። በዚህ ዐይነቱ ኃጢአት ላይ ወደቀ፤ ታዲያ እኛስ የእናንተን ምሳሌነት መከተልና የባዕዳን አገሮች ሴቶችን በማግባት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ ይገባናልን?” ከሊቀ ካህናቱ ከኤልያሺብ ልጆች አንዱ ዮያዳዕ ነበር፤ ነገር ግን ከእርሱ ልጆች አንዱ የቤትሖሮን ከተማ ነዋሪ የሆነውን የሰንባላጥን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር፤ ስለዚህም ዮያዳዕ ኢየሩሳሌምን ለቆ እንዲወጣ አደረግሁ። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፥ ይህ ሕዝብ ክህነትን፥ የክህነትን ሥርዓትንና አንተ ከካህናትና ከሌዋውያን ጋር ያደረግኸውን ቃል ኪዳን እንዴት እንዳረከሰ ተመልከት! ከባዕድ አገር ርኲሰት ራሳቸውን እንዲያነጹ አደረግሁ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው የሚፈጽሙትን ተግባር ዐውቀው የሚሠሩበትን ደንብ ሁሉ አዘጋጀሁ። መሥዋዕት የሚቃጠልበትን ማገዶ በተወሰነው ክፍለ ጊዜ ሁሉ ማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ አደራጀሁ፤ ሰዎቹም ከሚሰበስቡት ሰብል ሁሉ ከእህሉም ሆነ ከፍራፍሬው በመጀመሪያ የደረሰውን እንዴት ማቅረብ እንደሚገባቸው አዘጋጀሁ። አምላኬ ሆይ! ይህን ሁሉ አስብ፤ ይህን በማድረጌም ቸርነት አድርግልኝ።