የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 12

12
የካህናትና የሌዋውያን ስም ዝርዝር
1ከሰላትያል ልጅ ከዘሩባቤልና ከሊቀ ካህናቱ ከኢያሱ ጋር ከምርኮ የተመለሱት የካህናትና የሌዋውያን ስም ዝርዝር ከዚህ የሚከተለው ነው፤
2-7ካህናት፦
ሠራያ፥ ኤርምያስ፥ ዕዝራ፥
አማርያ፥ ማሉክ፥ ሐጡሽ፥
ሸካንያ፥ ረሑም፥ መሬሞት፥
ዒዶ፥ ጊነቶን፥ አቢያ፥
ሚያሚን፥ መዓድያ፥ ቢልጋ፥
ሸማዕያ፥ ዮያሪብ፥ ይዳዕያ፥
ሳሉ፥ ዓሞክ፥ ሒልቂያና ይዳዕያ።
እነዚህ ሰዎች በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ ዘመን የወገኖቻቸው ካህናት መሪዎች የነበሩ ናቸው።
8ሌዋውያን፦
የምስጋና መዝሙር ኀላፊዎች የነበሩት ሌዋውያን ኢያሱ፥ ቢኑይ፥ ቃድሚኤል፥ ሼሬብያ፥ ይሁዳና ማታንያ ነበሩ።
9ባቅቡቅያ፥ ዑኖና ሌሎችም ሌዋውያን ወንድሞቻቸው ከእነርሱ ጋር በመቀባበል ይዘምሩ ነበር።
የሊቀ ካህናቱ የኢያሱ ዘሮች
10ኢያሱ ዮያቂምን ወለደ፤ ዮያቂም ኤልያሺብን ወለደ፤ ኤልያሺብ ዮያዳዕን ወለደ፤ 11ዮያዳዕ ዮናታንን ወለደ፤ ዮናታን ያዱዓን ወለደ።
የካህናት ጐሣ አለቆች
12-21ዮያቂም ሊቀ ካህናት በነበረበት ዘመን ከዚህ የሚከተሉት ካህናት፥ የካህናት ጐሣዎች አለቆች ነበሩ፦
ካህኑ ጐሣው።
መራያ ሠራያ።
ሐናንያ ኤርምያስ።
መሹላም ዕዝራ።
የሆሐናን አማርያ።
ዮናታን መሉኪ።
ዮሴፍ ሸካንያ።
ዓድና ሓሪም።
ሔልቃይ መራዮት።
ዘካርያስ ዒዶ።
መሹላም ጊነቶን።
ዚክሪ አቢያ።
ሚንያሚን #12፥12 በዕብራይስጥ በዚህ ቦታ የሰውዬው ስም የለም። ፒልጣይ ሞዓዲያ።
ሻሙዐ ቢልጋ።
የሆናታን ሸማዕያ።
ማትናይ ዮያሪብ።
ዑዚ ይዳዕያ።
ቃላይ ሳላይ።
ዔቤር ዓሞቅ።
ሐሻብያ ሒልቂያ።
ናትናኤል ይዳዕያ።
የካህናትንና የሌዋውያንን ቤተሰቦች ስም ዝርዝር የሚገልጥ መዝገብ
22ኤልያሺብ፥ ዮያዳዕ፥ ዮናታንና ያዱዐ ተብለው የሚጠሩት ሊቃነ ካህናት በኖሩበት ዘመን የሌዋውያንና የካህናት ቤተሰብ አለቆች ተለይተው የሚታወቁበት መዝገብ ተዘጋጅቶ ነበር፤ ይህም መዝገብ የተዘጋጀው ዳርዮስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነበት ዘመን ነበር።
23ይሁን እንጂ የሌዋውያን ቤተሰብ አለቆች በግልጽ መዝገብ የታወቁት የኤልያሺብ የልጅ ልጅ የሆነው ዮናታን በሕይወት እስከ ኖረበት ዘመን ብቻ ነበር።
በቤተ መቅደስ የአገልግሎት አመዳደብ
24ሌዋውያኑ በሐሻብያ፥ በሼሬብያ፥ በኢያሱ፥ በቢኑይና በቃድሚኤል መሪነት በሁለት ቡድኖች ተከፈሉ። ሁለቱም ቡድኖች የእግዚአብሔር ሰው የሆነ ንጉሥ ዳዊት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እየተቀባበሉ የምስጋና መዝሙር በማቅረብ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
25በቤተ መቅደሱ ቅጽር በር አጠገብ የተሠሩትን የዕቃ ግምጃ ቤቶች የሚጠብቁ ዘበኞችም ማታንያ፥ ባቅቡቅያ፥ አብድዩ፥ መሹላም፥ ጣልሞንና ዓቁብ ተብለው የሚጠሩት ነበሩ።
26እነዚህም የኢዮጼዴቅ የልጅ ልጅ የሆነው የኢያሱ ልጅ ዮያቂም፥ አገረ ገዢው ነህምያ ካህኑና የሕግ ሊቁ ዕዝራ በነበሩበት ዘመን የተመደቡ አገልጋዮች ነበሩ።
ለኢየሩሳሌም ከተማ ቅጽር የምረቃ በዓል መደረጉ
27የኢየሩሳሌም ከተማ ቅጽር የምረቃ በዓል በተከበረበት ዕለት ሌዋውያኑ በጸናጽል፥ በበገናና በመሰንቆ በዓሉን እንዲያከብሩ ከየሚኖሩበት ስፍራ ተፈልገው መጡ። 28ይህንንም በዓል ለማክበር የሌዋውያኑ ቤተሰቦች መዘምራን ሁሉ ሰፍረው ከነበሩበት ከኢየሩሳሌም አካባቢና በነጦፋ ከሚገኙት ታናናሽ ከተሞች፥ 29ከቤትጊልጋል፥ ከጌባዕና ከዓዝማዌት ተሰብስበው መጡ፤ 30ካህናቱና ሌዋውያኑም ስለ ሕዝቡ ራሳቸው ስለ ከተማይቱ በሮችና ስለ ቅጽሩ የማንጻትን ሥርየት ፈጸሙ።
31እኔም ነህምያ የይሁዳን መሪዎች በቅጽሩ ላይ እንዲወጡ ካደረግሁ በኋላ ሁለት ታላላቅ የመዘምራን ቡድን የምስጋና መዝሙር እንዲዘምሩ አደረግሁ፤
የመጀመሪያው ቡድን በቅጽሩ ግንብ አናት ላይ በስተቀኝ በኩል ወደሚገኘው ወደ ጒድፍ መጣያው የቅጽር በር በኩል አለፈ፤ 32ሆሻዕያና የይሁዳ መሪዎች ተከተሉአቸው። 33-35ዐዛርያ፥ ዕዝራ፥ መሹላም፥ ይሁዳ፥ ብንያም፥ ሸማዕያና ኤርምያስ ተብለው የሚጠሩት ካህናትም በሰልፍ አለፉ፤ ቀጥሎም እምቢልታ የሚነፉ ጥቂት ካህናትና እንዲሁም ዘካርያስ የዮናታን ልጅ የሸማዕያ ልጅ፥ የማታንያ ልጅ፥ የሚክያን ልጅ፥ የዛኩር ልጅ የአሳፍ ልጅ አለፉ። 36የራሱ ጐሣ አባላት የነበሩት ሸማዕያ፥ ዐዛርኤል፥ ሚለላይ፥ ጊለላይ፥ ማዓይ፥ ናትናኤል፥ ይሁዳና ሐናኒ የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ይዘምርበት የነበረውን የሙዚቃ መሣሪያ ሁሉ ተሸክመው ተከተሉት፤ የዚህንም ቡድን ሰልፍ የሚመራው የሕግ ሊቁ ዕዝራ ነበር። 37ወደ ውሃው ምንጭ በር እንደ ደረሱም ወደ ዳዊት ከተማ አቅንተው በቅጽሩ ላይ ያሉትን ደረጃዎች በመውጣትና የዳዊትን ቤተ መንግሥት በማለፍ ከከተማይቱ በስተምሥራቅ ወደሚገኘው ወደ ውሃ ቅጽር በር ተመለሱ።
38ሌላው የመዘምራን ቡድን ሰልፍ የቅጽሩን ግንብ ጫፍ በመከተል ወደ ግራ በኩል አለፈ፤ እኔም ከሕዝቡ እኩሌታ ጋር ይህንኑ የቡድን ሰልፍ እከተል ነበር፤ የእቶኑንም ግንብ አልፈን ወደ ሰፊው ቅጽር ግንብ ደረስን። 39ከዚያም አልፈን የኤፍሬም ቅጽር በር፥ የይሻና ቅጽር በር፥ የዓሣ ቅጽር በር ተብለው ወደተሰየሙትና የሐናንኤል ግንብ የመቶዎቹ ግንብና የበጎች ቅጽር በር ተብለው ወደሚጠሩት ስፍራዎች መጣን፤ ሰልፋችንንም ያበቃነው ለቤተ መቅደሱ ቅርብ ወደ ሆነው የዘበኞች ቅጽር በር ወደሚባለው ቦታ ስንደርስ ነበር።
40በዚህም ሁኔታ የሁለቱም ቡድኖች ሰልፍ እግዚአብሔርን በመዝሙር በማመስገን ወደ ቤተ መቅደሱ ክልል ደረሰ፤ አብረውኝም ከነበሩት መሪዎች ጋር በተጨማሪ፥ 41የእኔ ቡድን ሰልፍ ከዚህ የሚከተሉትን እምቢልታ የሚነፉ ካህናትን የሚጨምር ነበር፤ እነርሱም ኤልያቄም፥ መዕሤያ፥ ሚንያሚን፥ ማካያ፥ ኤልዮዔናይ፥ ዘካርያስና ሐናንያ ሲሆኑ፥ 42እነርሱንም ደግሞ መዕሤያ፥ ሸማዕያ፥ አልዓዛር፥ ዑዚ፥ የሆሐናን፥ ማልኪያ፥ ኤላምና ኤዜር ተከትለዋቸው ይጓዙ ነበር፤ እንደ ቆምንም መዘምራኑ በይዝራሕያ እየተመሩ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ዘመሩ።
43በዚያም ዕለት ብዙ መሥዋዕት ቀረበ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔር ደስ ስላሰኛቸው ታላቅ ሐሴት አደረጉ፤ ሴቶችም፥ ልጆችም አብረው ተደስተዋል፤ በኢየሩሳሌም የነበረው የእልልታቸው ድምፅ እስከ ሩቅ ድረስ ይሰማ ነበር።
ለቤተ መቅደስ መገልገያ የሚቀርብ አስተዋጽዖ
44በዚያም ጊዜ ለቤተ መቅደስ መገልገያ የሚደረገውን አስተዋጽዖ እንዲሁም ከዐሥር አንዱን፥ በየዓመቱ በመጀመሪያ የሚደርሰውን እህልና ፍራፍሬ በማከማቸት የዕቃ ቤት ክፍሎችን የሚጠብቁ ኀላፊዎች ተሾሙ፤ እነዚህም ሰዎች በልዩ ልዩ ከተሞች አቅራቢያ ከሚገኙ የእርሻ ቦታዎች ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የተመደበውን አስተዋጽዖ የመሰብሰብ ኀላፊነት ነበራቸው፤ የይሁዳም ሕዝብ በሙሉ በካህናቱና በሌዋውያኑ እጅግ ደስ ብሎአቸው ነበር። 45የይሁዳም ሕዝብ ተደስቶ የነበረው እነርሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት መፈጸም የሚገባውን ደንብና የማንጻት ሥርዓት በማከናወናቸው ነበር፥ የቤተ መቅደሱ መዘምራንና የቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎችም ዳዊትና ልጁ ሰሎሞን በመደቡት ሥርዓት መሠረት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ፈጸሙ። #1ዜ.መ. 25፥1-8፤ 26፥12። 46ከንጉሥ ዳዊትና የመዘምራን አለቃ ከነበረው አሳፍ ዘመንም ጀምሮ ለመዘምራንና ለማኅሌታዊ ዜማ መሪዎች ነበሩአቸው። 47በዘሩባቤልና በነህምያ ዘመን መላው እስራኤላውያን ለቤተ መቅደሱ መዘምራንና ለዘብ ጠባቂዎቹ የየዕለት ድርሻቸውን ይሰጡ ነበር፤ ሌዋውያኑም የአሮን ተወላጁን ድርሻ ይሰጡ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ