የማርቆስ ወንጌል 9:1-13

የማርቆስ ወንጌል 9:1-13 አማ05

ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ አሁን እዚህ ካሉት መካከል አንዳንዶች የእግዚአብሔር መንግሥት በታላቅ ኀይል ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አሉ፤” አላቸው። ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ ወደ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ፤ በፊታቸውም መልኩ ተለወጠ። ልብሱ እጅግ አንጸባረቀ፤ በዓለም ላይ ማንም አጣቢ ያን ያኽል ሊያነጣ እስከማይችል ድረስ ነጭ ሆነ። በዚያን ጊዜ ኤልያስና ሙሴ ተገልጠው ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! እዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት እጅግ ደንግጠው ስለ ነበር ጴጥሮስ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፦ “የምወደው ልጄ ይህ ነው! እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ ተሰማ ወዲያውም ዞር ብለው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል አዘዛቸው። ቃሉንም ሰምተው በልባቸው ያዙት፤ ይሁን እንጂ “ይህ ከሞት መነሣት ምን ማለት ይሆን?” እያሉ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። እነርሱም፦ “የሕግ መምህራን መጀመሪያ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ስለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እርግጥ ነው፤ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያስተካክላል፤ ይሁን እንጂ፥ የሰው ልጅ ከባድ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚናቅ የተጻፈው እንዴት ነው? እኔ ግን ኤልያስ ቀደም ብሎ መጥቶአል፤ ሰዎችም ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል” እላችኋለሁ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች