ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ የሕግ መምህራን ወደ ኢየሱስ መጥተው በዙሪያው ተሰበሰቡ። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ በሥርዓት ባልነጻ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩአቸው። ፈሪሳውያንና የቀሩትም አይሁድ የሽማግሌዎችን ወግ በመጠበቅ እጃቸውን በሥርዓቱ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር። እንዲሁም ከገበያ ሲመለሱ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር፤ ዋንጫን፥ ማሰሮን፥ የናስ ዕቃዎችንና አልጋን፥ እንደማጠብ ያለ፥ ሌላም ብዙ ወግ ይጠብቁ ነበር። ስለዚህ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን፥ “ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ወግ በመጣስ፥ ስለምን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ ግብዞች! ኢሳይያስ ስለ እናንተ፥ ‘ይህ ሕዝብ በአፉ ብቻ ያከብረኛል እንጂ ልቡ ከእኔ የራቀ ነው! ሰው ሠራሽ ሥርዓትን እንደ እግዚአብሔር ሕግ አድርገው እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል!’ ብሎ የተናገረው ትንቢት ትክክል ነው፤ “ስለዚህ እናንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ወጋችሁን ለመጠበቅ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትተዋላችሁ፤ ሙሴ፦ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞም በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ ክፉ የሚናገር ሰው በሞት ይቀጣ፤’ ይላል። እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፤ ‘አንድ ሰው ለአባቱ ወይም ለእናቱ በመርዳት ፈንታ ለአባቱና ለእናቱ ማድረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ያቀረብኩት መባ ነው፤’ ቢላችሁ፥ አባትና እናቱን ከመርዳት ነጻ ታደርጉታላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንዲሁም ይህን የመሳሰለ ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።” ሕዝቡንም እንደገና ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ሁላችሁም በማስተዋል አዳምጡኝ፤ ሰውን የሚያረክሰው፥ ከሰው የሚወጣው ነገር ነው እንጂ ከውጪ ወደ ሰው የሚገባውስ አያረክሰውም! [እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”] ኢየሱስ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተም ደግሞ ይህን አታስተውሉምን? ከውጪ ወደ ሰው የሚገባ ነገር ሰውን ምንም እንደማያረክሰው አይገባችሁምን? በሆድ በኩል ተላልፎ ወደ ውጪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይሄድም፤”። በዚህም ኢየሱስ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጸ። ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “ሰውን የሚያረክሱት ከሰው ልብ የሚወጡት ነገሮች ናቸው። እነርሱም፦ ክፉ ሐሳብ፥ ዝሙት፥ ስርቆት፥ ሰውን መግደል፥ አመንዝራነት፥ ስግብግብነት፥ ክፋት፥ አታላይነት፥ ስድነት፥ ምቀኝነት፥ ሐሜተኛነት፥ ትዕቢት፥ ግዴለሽነት ናቸው። ይህ ሁሉ ክፉ ነገር ከሰው ልብ ይወጣል፤ ሰውንም ያረክሰዋል።” ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በጢሮስ ከተማ አጠገብ ወዳለው መንደር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤትም ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም ሰው እንዳያውቅ ፈለገ፤ ይሁን እንጂ ሊሰወር አልተቻለውም። ልጅዋ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ ኢየሱስ ሰምታ ወዲያውኑ መጣችና በእግሩ ሥር ወደቀች። ሴትዮዋም ከሲሮፊኒቃውያን ወገን የሆነች ግሪካዊት ነበረች፤ እርስዋ ከልጅዋ ጋኔን እንዲያወጣላት ኢየሱስን ለመነችው። ኢየሱስ ግን፥ “የልጆችን ምግብ ወስዶ ለውሾች መስጠት አይገባምና እስቲ ልጆቹ አስቀድመው ይጥገቡ፤” አላት። እርስዋም “እርግጥ ነው ጌታዬ፤ ግን ውሾችም እኮ በገበታ ሥር ሆነው ልጆች ሲበሉ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤” ስትል መለሰችለት። ስለዚህ ኢየሱስ፥ “በዚህ አነጋገርሽ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል፤ እንግዲህ ወደ ቤትሽ ሂጂ!” አላት። እርስዋም ወደ ቤትዋ በተመለሰች ጊዜ ልጅዋን ጋኔኑ ለቋት በአልጋ ላይ በደኅና ተኝታ አገኘቻት።
የማርቆስ ወንጌል 7 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 7:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos