የማርቆስ ወንጌል 6:33-56

የማርቆስ ወንጌል 6:33-56 አማ05

ይሁን እንጂ እነርሱ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቁአቸው፤ ከየከተማውም ወጥተው በእግር እየሮጡ ቀደሙአቸውና ወደ እነርሱ ተሰበሰቡ። ኢየሱስ ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሰዎችን አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በመሆናቸውም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። ጊዜው እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ቦታው በረሓ ነው፤ ጊዜውም መሽቶአል፤ የሚበሉት የላቸውምና በአካባቢው ወዳሉት ገጠሮችና መንደሮች ሄደው ምግብ እንዲገዙ እነዚህን ሰዎች አሰናብታቸው።” ኢየሱስ ግን፦ “የሚበሉትን እናንተ ስጡአቸው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ታዲያ፥ ሄደን የሚበሉትን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር ገዝተን እንስጣቸውን?” አሉ። እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሂዱና እዩ፤” አላቸው፤ አይተውም “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አለ፤” አሉት። ኢየሱስም ሕዝቡን በቡድን ከፋፍለው፥ በለመለመው መስክ ላይ እንዲያስቀምጡአቸው ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። ስለዚህ ሕዝቡ በመቶና በኀምሳ ተከፋፍለው በቡድን ተቀመጡ። ኢየሱስም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እንዲሁም ሁለቱን ዓሣ ለሁሉም አከፋፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ። ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ሰበሰቡ። እንጀራውን የበሉ ወንዶች ቊጥር አምስት ሺህ ያኽል ነበር። ኢየሱስ ወዲያውኑ ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ሆነው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ ተሻግረው እንዲቀድሙት አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ከእነርሱ ተለይቶ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ጀልባዋ በባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱ ግን ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። ደቀ መዛሙርቱ ከወደፊታቸው በሚነፍሰው ነፋስ ምክንያት መቅዘፍ ተቸግረው ሲጨነቁ አያቸው፤ ከሌሊቱም ከዘጠኝ እስከ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ፤ አልፎአቸውም ሊሄድ ነበር። ነገር ግን እነርሱ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲሄድ አይተው መንፈስ መስሎአቸው ጮኹ። ሁሉም ባዩት ጊዜ ደነገጡ። እርሱ ግን ወዲያውኑ፦ “አይዞአችሁ! እኔ ነኝ! አትፍሩ!” አላቸው፤ ወደ ጀልባውም ገብቶ፥ ከእነርሱ ጋር በሆነ ጊዜ ነፋሱ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ በጣም ተደነቁ። ታዲያ፥ ልባቸው ደንዝዞ፥ የእንጀራውን ተአምር ሳያስተውሉ ቀርተው ነው እንጂ ይህ ነገር ባላስገረማቸውም ነበር። ባሕሩን ተሻግረው፥ ወደ ጌንሳሬጥ ደረሱ፤ ጀልባዋን ወደ ምድር አስጠግተው አሰሩ፤ ከጀልባ እንደወረዱ ወዲያውኑ ሰዎች ኢየሱስን ዐወቁት፤ እነርሱም በዚያ አገር ዙሪያ እየተራወጡ ኢየሱስ ወዳለበት ስፍራ ሁሉ በሽተኞችን በአልጋ ተሸክመው ያመጡ ጀመር። በየሄደበትም ስፍራ ሁሉ በመንደር፥ በከተማ፥ በገጠርም በሽተኞችን ወደ አደባባይ እያወጡ በእርሱ ፊት ያቀርቡአቸው ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ እንዲነኩ ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች